አዲስ አበባ፤ሰኔ 3/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት በ2018 በጀት ዓመት 8 ነጥብ 9 በመቶ እድገት እንደሚያሳይ እንደሚጠበቅ የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ተናገሩ።
የ2018 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት 1 ነጥብ 93 ትሪሊዮን ብር ሆኖ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቧል።
ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 35ኛ መደበኛ ስብሰባ የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ያቀረቡትን የፌዴራል መንግሥት የ2018 በጀት ዓመት ረቂቅ የበጀት መግለጫ አዳምጧል፡፡
በመግለጫቸው መንግስት ተግባራዊ ያደረገው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አፈጻጸም ስኬታማ ውጤት በማምጣቱና የግል ኢንቨስትመንት በመጨመሩ ተግባራዊነቱ በቀጣዮቹ ዓመታትም ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
በዚህም በማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸም የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን በተሟላ ሁኔታ ለማቃለልና የአገሪቷን ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ዘላቂና ቀጣይነት በማረጋገጥ የብልጽግና ጉዞውን ስኬታማ ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የመካከለኛ ዘመን የማክሮ ኢኮኖሚና ፊዚካል ማዕቀፍን በመከተል አጠቃላይ የፌዴራል መንግስት የ2018 ጠቅላላ ወጪ በጀት 1 ነጥብ 93 ትሪሊዮን ብር ሆኖ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡
ይህም በ2017 በጀት ዓመት የተጨማሪ በጀትን ጨምሮ ከጸደቀው የወጪ በጀት የ34 ነጥብ 4 በመቶ እድገት አለው ብለዋል።
ከወጪ በጀቱ ውስጥ 1 ነጥብ 2 ትሪሊዮን ብር ለመደበኛ ወጪ፣ 415 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ለካፒታል ወጪ፣ 315 ቢሊዮን ብር ለክልሎች ድጋፍና 14 ቢሊዮን ብር ለዘላቂ ልማት ግቦች የተመደበ መሆኑን አብራርተዋል።
ጠቅላላ ከተያዘው የካፒታል በጀት ውስጥ 74 ነጥብ 5 በመቶ ድርሻ ያላቸው ከፍተኛ ትኩረት ለተሰጣቸው ዘርፎች መመደባቸውን ገልጸዋል።
በ2018 በጀት ዓመት የመንግስትን ገቢ አሰባሰብ ለማሳደግ የብሔራዊ መካከለኛ ዘመን የገቢ ስትራቴጂን አጠናክሮ መቀጠል አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው፤ አዳዲስ የታክስ ፖሊሲዎችን በስራ ላይ ለማዋል ይሰራል ነው ያሉት።
በገቢ በኩል በ2018 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግስት ጠቅላላ ገቢ የውጭ እርዳታን ጨምሮ 1 ነጥብ 5 ትሪሊዮን ብር እንደሚሆን መገመቱን አመልክተዋል።
በሁለተኛው የአገር በቀል ምጣኔ ሃብት መርሃ ግብር የተቀመጡ ማሻሻያዎች በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፎች ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ኢኮኖሚው በ2018 በጀት ዓመት የተሻለ እድገት እንደሚያሳይ ገልጸዋል።
በዚህም የኢትዮጵያ የምጣኔ ሃብት እድገት በ2018 በጀት አመት የ8 ነጥብ 9 በመቶ እድገት እንደሚያስመዘግብም ይጠበቃል ብለዋል።
የምክር ቤቱ አባላት በሰጡት አስተያየት፤ ለ2018 በጀት ዓመት የተዘጋጀው ረቂቅ በጀት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ውጤታማ ለማድረግ መታየት አለበት ያሏቸውን ጉዳዮች አንስተዋል።
መንግስት አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ከመጀመር ይልቅ ነባር ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ በሰጠው ትኩረት ላይ ለተነሳውና ለሌሎች ጥያቄዎች ሚኒስትሩ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በጀቱ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን በተሳካ ሁኔታ ተግባራዊ ለማድረግ ሚናው ከፍተኛ በመሆኑ ባለበጀት መስሪያ ቤቶች የተመደበላቸውን በጀት ለታለመለት አላማ ማዋል እንዳለባቸው ሚኒስትር አህመድ ሽዴ አሳስበዋል።
ምክር ቤቱ በረቂቅ በጀቱ ላይ የተሰጡ አስተያየቶችን በማከል በዝርዝር እንዲያየው ለፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶታል።
አዲስ አበባ፤ የካቲት 21/2017(ኢዜአ)፡- የምግብ ዋስትና እና ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ለነገ የሚተው የምርጫ ጉዳይ ባለመሆኑ በልዩ ትኩረት መረባረብ እንደሚገባ...
Feb 28, 2025
ሐረር፤ የካቲት 16/2017(ኢዜአ)፦ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ ሁሉን አቀፍ ስራዎች የህዝቡን ተጠቃሚነት ያሳደጉ መሆናቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ ጥር 30/2017(ኢዜአ)፦የየካቲት ወር የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ በጥር ወር በነበረበት የሚቀጥል መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስ...
Feb 8, 2025