የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

ኢትዮጵያ አነስተኛ ማሳ ያላቸው አርሶ አደሮች ምርታማነትን እንዲያሳድጉ የፋይናንስና ኢንሹራንስ አገልግሎት እያቀረበች ነው

Jun 11, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ሰኔ 4/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ የሆኑና በአነስተኛ ማሳ የሚያመርቱ አርሶና አርብቶ አደሮችን የፋይናንስ አቅም በማሳደግ ምርትና ምርታማነታቸው እንዲጨምር ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ገለፁ።

በአነስተኛ ማሳ የሚያመርቱ አርሶአደሮች የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነትና የፋይናንስ አቅርቦት ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው።

የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በውይይቱ መክፈቻ፥ ኢትዮጵያ በ10 ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅዷ ለግብርና ዘርፍ በሰጠችው ትኩረት ምርትና ምርታማነትን የበለጠ ማሳደግ መቻሏን አንስተዋል።

በዚህም ለረጅም ዓመታት ሀገራዊ የስንዴ ፍጆታን ሙሉ ለሙሉ በሀገር ውስጥ ምርት በመሸፈን ከውጭ የሚገባውን አስቀርተናል ነው ያሉት።

አካታችና የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚያስችል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መደረጉንም ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በየዓመቱ የምትተክላቸው ችግኞች ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ በምግብ ራስን ለመቻል የምታደርገውን ጥረት እያገዘ ነው ብለዋል።

በሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭም የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥና የበርካታ ዜጎችን የአመጋገብ ሥርዓት በመቀየር ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ነው የገለፁት።

በአነስተኛ ማሳ የሚያመርቱ አርሶና አርብቶ አደሮች ለአየር ንብረት ለውጥ የበለጠ ተጋላጭ መሆናቸውን ያነሱት ሚኒስትሩ፥ ኢትዮጵያ ተፅዕኖውን ለመቋቋም አሰራር መዘርጋቷን ገልፀዋል።

የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲው አነስተኛ ማሳ ያላቸው አርሶ አደሮች በቀላሉ የፋይናንስ ብድር አቅርቦት እንዲያገኙ ዕድል መስጠቱን አመልክተዋል።

በዚህም ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ የሆኑ አርሶና አርብቶ አደሮች የፋይናንስና የኢንሹራንስ አቅማቸውን የበለጠ እንዲያጠናክሩ በማገዝ ምርትና ምርታማነታቸው እንዲጨምር ድጋፍ እየተደረገ ነው ብለዋል።

የገጠር ልማትን ለማረጋገጥ፣የህዝቡን ኑሮ ለማሻሻል፣ የፋይናንስ አቅርቦትን ተደራሽነት የበለጠ ለማጠናከር የመረጃ አያያዝ ስርዓትን የማዘመን ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ተናግረዋል።

አካታች የፋይናንስ ሥርዓት በመዘርጋት የገጠር ልማትን ለማረጋገጥ የባለድርሻ አካላት ትብብርና ቅንጅታዊ አሰራር የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.