የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

የኦዲት ባለድርሻ አካላት ፎረም የቁጥጥር ስርዓትን በማጠናከር ተጠያቂነትን ለማስፈን አስቻይ ሁኔታ ፈጥሯል-ቋሚ ኮሚቴው

Jun 12, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 4/2017(ኢዜአ)፡- የኦዲት ባለድርሻ አካላት ፎረም የተቋማትን አሰራር በመፈተሽ የቁጥጥር ስርዓትን ለማጠናከርና ተጠያቂነትን ለማስፈን አስቻይ ሁኔታ መፍጠሩን የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስታወቀ።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኦዲት ባለድርሻ አካላት ፎረም የ2017 በጀት አመት አፈፃፀም ላይ ውይይት አካሒዷል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የሺመቤት ደምሴ (ዶ/ር) የኦዲት ባለድርሻ አካላት ፎረም እቅድ አፈጻጸም ማጠቃለያ ሪፖርት አቅርበዋል።

ቋሚ ኮሚቴው የፌዴራል ተቋማት በመንግስት የተመደበ በጀት አጠቃቀማቸውን፣ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች፣ ህጎች፣ የአሰራር ስርዓቶችንና እቅዶችን መፈተሽ ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ፎረሙ አስፈጻሚ ተቋማትና ሌሎች ቋሚ ኮሚቴዎች ለኦዲት ሪፖርት የሚሰጡት ትኩረት እንዲጨምር እድል መፍጠሩንም ተናግረዋል።

በዚህም በበጀት ዓመቱ ከኦዲት ግኝት ጋር ተያይዞ አስተያየት ከተሰጣቸው ተቋማት ውስጥ ለሶስት ተቋማት የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ እንዲሁም ለኃላፊዎች የገንዘብ ቅጣት እንዲጣልባቸው ማድረግ መቻሉን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ጨምሮ ለሰባት የመንግስት ተቋማት የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ እንዲደርሳቸው ተደርጓል ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ በተከናወኑ የኦዲት ግኝት ተግባራት ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት መቻሉንም ተናግረዋል።

ይህም የኦዲት ባለድርሻ አካላት ፎረም የተቋማትን አሰራር በመፈተሽ የቁጥጥር ስረዓትን ለማጠናከርና ተጠያቂነትን ለማስፈን አስቻይ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል።

በውይይቱ ላይ የተለያዩ የፌዴራል ተቋማት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.