የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

ችግር ፈቺ የፈጠራ ስራዎች "መፍጠር እና መፍጠን" የሚለውን አገራዊ እሳቤ ከዳር ለማድረስ ጉልህ አስተዋፅኦ እያበረከቱ ነው

Jun 20, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ሰኔ 12/2017(ኢዜአ)፦ችግር ፈቺ የፈጠራ ስራዎች "መፍጠር እና መፍጠን" የሚለውን አገራዊ እሳቤ ከዳር ለማድረስ ጉልህ አስተዋፅኦ እያበረከቱ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ ገለፁ።

"የሀሳብ ፈጠራ ለብሩህ ነገ" በሚል መሪ ሃሳብ ሲካሔድ የቆየው የንግድ ፈጠራ ሃሳብ ውድድር የማጠቃለያ መርኃ ግብር በዓድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ ይገኛል።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ በመርኃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልእክት እንደገለጹት፤ በአዲስ አበባ በሶስት ዙሮች በተካሄደው የንግድ ፈጠራ ሃሳብ ውድድር አበረታች ውጤት ተመዝግቧል።


ውድድሩ ወጣቱ ስራ ፈጣሪ፣ ተወዳዳሪና በአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ውስጥ የጎላ ተሳትፎ እንዲኖረው ከማስቻል ባለፈ በቴክኖሎጂ ዘርፍ ያለውን አቅም ለማውጣት እድል ፈጥሯል ብለዋል።

ወጣቶች የሚያመነጯቸውን ችግር ፈቺ የፈጠራ ሃሳቦች በዘላቂነት ጥቅም ላይ ለማዋል በትኩረት እየተሰራበት መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተለይም የሚበለጽጉ የፈጠራ ስራዎች ከአገር አልፎ አለም አቀፍ ተፈላጊነት እንዲኖራቸው መስራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

መንግስት በየወቅቱ ጥራታቸው፣ ደህንነታቸውና ችግር ፈቺ መሆናቸው የተረጋገጡና የተመረጡ የፈጠራ ስራዎችን ተግባራዊ ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

ለአብነትም የሃሳብ ፈጠራ ውድድሩ አንዱ ማሳያ መሆኑን ጠቁመው ይህም "መፍጠርና መፍጠን" የሚለውን አገራዊ እሳቤ ከዳር ለማድረስ ጉልህ አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል ነው ያሉት።


በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ስራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥራቱ በየነ በበኩላቸው፣ የወጣቶች የፈጠራ ስራዎች የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ተናግረዋል።


የፈጠራ ውጤቶቹ አገር አሻጋሪ ትውልድ እየተፈጠረ መሆኑን በተግባር ያሳያሉ ያሉት ምክትል ከንቲባው የፈጠራ ሃሳብ ውድድሩ ጠቃሚ የፈጠራ ውጤቶች ይፋ የሚደረጉበት መሆኑን አስታውቀዋል።

በውድድሩ የተሳተፉ የፈጠራ ሃሳብ ባለቤቶች በቀጣይ የፋይናንስ አቅርቦትና የገበያ ትስስር የሚፈጠርላቸው መሆኑን አረጋግጠዋል።

በውድድሩ 145 ወጣቶች የተሳተፉ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 15 ቱ ከተማዋን ወክለው በፌደራል ደረጃ በሚደረጉ ተመሳሳይ ውድድሮች እንደሚሳተፉ ጠቅሰዋል።

እየተካሄደ ባለው ውድድር ምርጥ አምስት ተወዳዳሪዎች ተሸላሚ እንደሚሆኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.