የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

ለዘላቂ ልማትና ለሀገር የብልጽግና ጉዞ መረጋገጥ የፈጠራ ስራ ወሳኝ ነው

Jun 20, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 12/2017(ኢዜአ)፦ ለዘላቂ ልማትና ለሀገር የብልጽግና ጉዞ መረጋገጥ የፈጠራ ስራ ወሳኝ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሀላፊ ጃንጥራር አባይ ገለጹ።

"የሀሳብ ፈጠራ ለብሩህ ነገ" በሚል መሪ ሃሳብ ሲካሔድ የቆየው የንግድ ፈጠራ ሃሳብ ውድድር የማጠቃለያ መርኃ ግብር በአድዋ ድል መታሰቢያ ተካሂዷል።


አቶ ጃንጥራር አባይ በመርኃ ግብሩ እንደገለጹት በአዲስ አበባ በሶስት ዙሮች በተካሄደው የንግድ ፈጠራ ሃሳብ ውድድር አበረታች ውጤት ተመዝግቧል።

ውድድሩ ወጣቱ ስራ ፈጣሪ፣ ተወዳዳሪ እና በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ውስጥ የጎላ ተሳትፎ እንዲኖረው ከማስቻል ባለፈ በቴክኖሎጂ ዘርፍ ያለውን አቅም ለማውጣት ዕድል ፈጥሯል ብለዋል።

ለዘላቂ ልማትና ለሀገር የብልጽግና ጉዞ መረጋገጥ የፈጠራ ስራ ወሳኝ ነው ያሉት ምክትል ከንቲባው በውድድር ማሸነፍና ሽልማት ማግኘት ብቻ የመጨረሻ ግብ መሆን የለበትም ብለዋል።

መንግስት በየወቅቱ ጥራታቸው፣ ደህንነታቸውና ችግር ፈቺ መሆናቸው የተረጋገጡና የተመረጡ የፈጠራ ስራዎችን ተግባራዊ ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

ለአብነትም የሃሳብ ፈጠራ ውድድሩ አንዱ ማሳያ መሆኑን ጠቁመው ይህም "መፍጠርና መፍጠን" የሚለውን ሀገራዊ እሳቤ ከዳር ለማድረስ ጉልህ አስተዋፅኦ አለው ብለዋል።

ውድድሩን በአሸናፊነት ያጠናቀቁ የፈጠራ ስራ ባለቤቶች በበኩላቸው ውድድሩ የፈጠራ ሃሳቦቻቸውን ተግባራዊ ለማድረግ ምቹ ዕድል የሚፈጥር ነው ሲሉ ገልጸዋል።


ውድድሩን በአንደኛ ደረጃ ያጠናቀቀው ወጣት ያዕቆብ በላይነህ የፕላስቲክ ኮዳን መልሶ በመጠቀም ፊላሚንት የተባለ ግብዓትና 3D ፕሪንት ማሽን መፍጠር መቻሉን ገልጿል።

ሽልማቱ የፈጠራ ሃሳቡን ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚያግዘው ገልጾ ውድድሩ የፈጠራ ሃሳብ ያላቸው ወጣቶችን የሚያነሳሳ መሆኑን አስታውቋል።

ባቀረበው የሎጂስቲክ መተግበሪያ ሁለተኛ የወጣው ወጣት ፈልመታ አብደታ መተግበሪያው የጭነት መኪናዎችንና ተጠቃሚውን በቀላሉ ማገናኘት የሚያስችል በመሆኑ ለኮንስትራክሽን ዘርፍ ጠቃሚ ነው ብሏል።


የመድሃኒት መደብሮች ያላቸውን መድሃኒቶች ማሳወቅ የሚያስችል መተግበሪያን በማበልጸግ ሶስተኛ ደረጃ ያገኘው ወጣት ማዕረግ ዘውዱ በበኩሉ መተግበሪያው መድሃኒት ፍለጋ የሚደረግ እንግልትን የሚያስቀር ነው ብሏል።

ይህ ውድድር ስራውን ይበልጥ ለማዳበር እንዳገዘው ገልጾ በውድድር የሚወጡ የፈጠራ ሃሳቦች ጥራታቸውንና ተአማኒነታቸውን እንዲጠብቁ አስቻይ ሁኔታን ይፈጥራል ብሏል።


በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ስራና ክህሎት ቢሮ ሀላፊ ጥራቱ በየነ በበኩላቸው የወጣቶች የፈጠራ ስራዎች የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ ብለዋል።

የፈጠራ ውጤቶቹ ሀገር አሻጋሪ ትውልድ እየተፈጠረ መሆኑን በተግባር እንደሚያሳዩ ጠቁመው የፈጠራ ሃሳብ ውድድሩ ጠቃሚ የፈጠራ ውጤቶችን ተግባራዊ ለማድረግ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን አስታውቀዋል።


በውድድሩ የተሳተፉ የፈጠራ ሃሳብ ባለቤቶች በቀጣይ የፋይናንስ አቅርቦትና የገበያ ትስስር እንደሚፈጠርላቸው አረጋግጠዋል።

በንግድ ፈጠራ ሃሳብ ውድድሩ 145 ወጣቶች የተሳተፉ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 15ቱ ከተማዋን ወክለው በፌደራል ደረጃ በሚደረጉ ተመሳሳይ ውድድሮች መሳተፍ ችለዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.