አዲስ አበባ፤ ሰኔ 15/2017(ኢዜአ)፦ በኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ የተመራ ከፍተኛ ልዑክ የአፍሪካና የአሜሪካ የቢዝነስ ጉባኤ ላይ ለመታደም በአንጎላ ርዕሰ መዲና ሉዋንዳ ገብቷል።
በፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ የተመራው ልዑክ ሉዋንዳ ሲደርስ በሀገሪቱ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል።
የዘንድሮውን የአፍሪካና የአሜሪካ የቢዝነስ ጉባኤ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር አሜሪካ አፍሪካን በተመለከተ የምትከተለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ድጋፍን መሰረት ካደረገው ወደ ንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ለመቀየር መወሰኑን ተከትሎ የሚካሄድ መሆኑ ልዩ ያደርገዋል።
ዛሬን ጨምሮ ለአራት ቀናት በሚካሄደው በዚህ ጉባኤ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች፣ ሚኒስትሮች፣ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የአሜሪካ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ የሁለቱም ወገን የቢዝነስ መሪዎችን ጨምሮ 1ሺህ 500 ተሳታፊዎች በጉባኤው ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ጉባኤው በአፍሪካና በአሜሪካ መካከል ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር በሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችና ዕድሎች ዙሪያ በመምከር ቀጣይ አቅጣጫዎችን እንደሚያስቀምጥ ታምኖበታል።
በጉባኤው ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ንግግር የሚያደርጉ ሲሆን ጎን ለጎንም የተለያዩ የሁለትዮሽ ውይይቶች እንደሚያደርጉ ኢዜአ ለማወቅ ችሏል።
በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ልዑክ አባላት በጉባኤው በፓናል ውይይትና በሌሎች ቁልፍ ስብሰባዎች ላይ ተሳትፎ ያደርጋል።
ኢትዮጵያ በውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋ በተለይም ለኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ በሰጠችው ትኩረት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ፣ የሁለትዮሽ የንግድ ትስስርን በማጠናከርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ለኢትዮጵያ ምርቶች አዳዲስ ገበያዎችን በማፈላለግ በኩል አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል።
መሰል ጉባኤዎችም ኢትዮጵያ በዘርፉ እያስመዘገበች ያለውን ውጤት ይበልጥ ከማጠናከር በዘለለ ሀገሪቱ በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ያላትን እምቅ አቅም ለማስተዋወቅና ጥቅም ላይ እንዲውል እድል በመፍጠር ትልቅ አበርክቶ እንደሚኖረው ይጠበቃል።
ይህም ኢትዮጵያ ገቢራዊ ያደረገችው የኢኮኖሚ ሪፎርም ተግባራዊነት በማቀላጠፍ የኢኮኖሚያዊ እድገቱን በማስቅጠል ትልቅ ሚና እንደሚኖረውም እንዲሁ።
አዲስ አበባ፤ የካቲት 21/2017(ኢዜአ)፡- የምግብ ዋስትና እና ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ለነገ የሚተው የምርጫ ጉዳይ ባለመሆኑ በልዩ ትኩረት መረባረብ እንደሚገባ...
Feb 28, 2025
ሐረር፤ የካቲት 16/2017(ኢዜአ)፦ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ ሁሉን አቀፍ ስራዎች የህዝቡን ተጠቃሚነት ያሳደጉ መሆናቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ ጥር 30/2017(ኢዜአ)፦የየካቲት ወር የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ በጥር ወር በነበረበት የሚቀጥል መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስ...
Feb 8, 2025