የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአገር ውስጥ መድሃኒት የማምረት አቅምን የሚያሳድጉ የምርምር ውጤቶችን እያፈለቀ ነው

Jun 25, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 17/2017(ኢዜአ)፦የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ምርምር ማዕከል በአገር ውስጥ መድሃኒት የማምረት አቅምን የሚያሳድጉ የምርምር ውጤቶችን እያፈለቀ መሆኑን አስታወቀ።

በሲዲቲ አፍሪካ ማዕከል የድራግ ዲቨሎፕመንት ቡድን መሪ ዶክተር በለጠ አደፍርስ ለኢዜአ እንደተናገሩት ማዕከሉ መድሃኒትን በአገር ውስጥ የማምረት አቅምን ለማሳደግ የሚደረጉ ጥረቶችን በምርምር እየደገፈ ይገኛል።

ሲዲቲ አፍሪካ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ውስጥ የሚገኝ የምርምር ማዕከል ሲሆን የህክምና ንጥረ ነገሮችን በምርምር ማውጣት የተቋቋመበት ዋና አላማ መሆኑን አስረድተዋል።

ማዕከሉ መድሃኒት፣ ክትባትና የመመርመሪያ ኪቶች በአገር ውስጥ እንዲሁም በአፍሪካ እንዲመረቱ ምርምር፣ የአቅም ግንባታ እንዲሁም የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት መድሃኒትን በአገር ውስጥ የማምረት አቅምን ለማሳደግ እየሰራች ሲሆን መድሃኒትን ለማምረት የሚያስፈልገው ንጥረ ነገር ከውጭ እንደሚገባ አስታውሰዋል።

የምርምር ውጤቶች መድሃኒት በአገር ውስጥ ለማምረት ከውጭ የሚገባውን ንጥረ ነገር በማስቀረት፣ የአገር ውስጥ የማምረት አቅምን ለማጠናከርና ተደራሽነትን ለማስፋት ትልቅ ፋይዳ አላቸው ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው ከውጭ የሚገባውን ንጥረ ነገር በምርምር በማውጣት በአገር ላይ የሚደርሰውን የምጣኔ ሀብት ጫና ለመቀነስና የማምረት አቅምን የበለጠ ለማሳደግ እየሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

እንደ ቡድን መሪው ገላጸ ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ሃብት በመጠቀም ቁስልን ለማከም እንዲሁም ለቆዳ እንክብካቤ የሚውሉ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለማምረት የሚያግዙ ንጥረ ነገሮችን ማዕከሉ በምርምር እያወጣ ይገኛል።

በመድሃኒት ዋጋ ላይ ከ60 እስከ 70 በመቶ የዋጋ ጭማሪን ከሚያስከትሉት አንዱ መድሃኒቱን ለማምረት ከውጭ የሚገባው ንጥረ ነገር መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም ማዕከሉ እያደረገ ያለው ምርምር መድሃኒትን በአገር ውስጥ የማምረት አቅምን በማሳደግ ወጪን ይቀንሳል ብለዋል።

የምርምር ውጤቶችን ወደ ምርት ለመቀየር በአዕምሯዊ ንብረት የማስመዝገብና ኢንቨስትመንት የማፈላለግ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.