ጎንደር ፤ ሰኔ 17/2017(ኢዜአ)፡- በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የጣና ሃይቅ ገባር ወንዞች በክረምቱ ወራት የሚያስከትሉትን የጎርፍ አደጋ መከላከል የሚያስችል 16 ኪሎ ሜትር የአፈር ግድብ ስራ መከናወኑን የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
የጽሕፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ ኑረዲን ሰኢድ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የጎርፍ ቅድመ መከላከል ስራው የተከናወነው በዞኑ የጣና ሀይቅ አዋሳኝ በሆኑት በምስራቅና ምዕራብ ደንቢያ ወረዳዎች በ6 ቀበሌዎች ውስጥ ነው፡፡
ባላፉት ሶስት ወራት በተከናወነው የጎርፍ መከላከል ስራ ድርማና ዳህና በተባሉ የጣና ሀይቅ ገባር ወንዞች ላይ በክልሉ መንግስት 10 ሚሊዮን ብር በጀት የአፈር ግድብ ስራ ማከናወን መቻሉን አውስተዋል።
በማሽነሪዎችና በህብረተሰቡ የጉልበት ተሳትፎ በተከናወነው የጎርፍ መከላከል ስራ በወንዞቹ ግራና ቀኝ ከፍታቸው አስከ አራት ሜትር የሆኑ የጎርፍ መከላከያ የአፈር ግድቦች መሰራታቸውን ተናግረዋል፡፡
የጎርፍ ቅድመ መከላከል ስራው በአካባቢዎቹ 960 አባወራዎችና እማወራዎችን፣ 3ሺህ ሄክታር የሚጠጋ የእርሻ ማሳንና 16ሺህ የሚጠጉ የቤት እንስሳትን ከአደጋ መታደግ የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል።
የአፈር ግድቡ ዘላቂ አገልግሎት እንዲሰጥም በየዓመቱ ችግኝ ተከላን ጨምሮ በስነ ህይወታዊ ዘዴዎች የማጠናከር ስራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።
የዳህና ወንዝ ክረምት በገባ ቁጥር ሰብሮ በመውጣት በመኖሪያ ቤታችንና በእርሻ ማሳችን ላይ ሰፊ ጉዳት ያደርስብን ነበር ያሉት ደግሞ በምዕራብ ደንቢያ ወረዳ የዋዋ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ታምራት ግዛቸው ናቸው፡፡
በየዓመቱ የሚከናወኑ የጎርፍ መከላከያ ግድቦች ከስጋት እየታደጓቸው መሆኑን ጠቁመው፤ ዘንድሮም ተመሳሳይ ተግባር በመከናወኑ ስጋት እንደሌለባቸው ተናግረዋል።
በምስራቅ ደንቢያ ወረዳ የጃንጓ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ጎሹ መልካሙ፤ የድርማ ወንዝ በየዓመቱ በሚያስከትለውን የጎርፍ መጥለቅለቅ አደጋ ለመቀነስ የመከላከያ ክትር መሰራቱ መልካም ነው ብለዋል።
የጎርፍ መከላከያ ግድቡ ዘላቂነት እንዲኖረውም ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን የአፈርና ውሃ እቅባ ስራ እያከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ክረምቱን ተከትሎ ሊከሰቱ የሚችሉ የተፈጥሮ አደጋዎችን መከላከልና ፈጣን ድጋፍ ለመስጠት የሚያስችል አብይ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
አዲስ አበባ፤ የካቲት 21/2017(ኢዜአ)፡- የምግብ ዋስትና እና ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ለነገ የሚተው የምርጫ ጉዳይ ባለመሆኑ በልዩ ትኩረት መረባረብ እንደሚገባ...
Feb 28, 2025
ሐረር፤ የካቲት 16/2017(ኢዜአ)፦ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ ሁሉን አቀፍ ስራዎች የህዝቡን ተጠቃሚነት ያሳደጉ መሆናቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ ጥር 30/2017(ኢዜአ)፦የየካቲት ወር የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ በጥር ወር በነበረበት የሚቀጥል መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስ...
Feb 8, 2025