አዲስ አበባ፤ ሰኔ 18/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ብሔራዊ የዲጂታል ፍኖተ ካርታና የዲጂታል ጤና ስራ ክፍሎችን በማደራጀት ፈጠራን እንደ ስትራቴጂክ ችግር መፍቻ መቀበሏ ውጤት ለማስመዝገብ ዓይነተኛ ሚና መጫወቱን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ሳህረላ አብዱላሂ ገለጹ።
ዓለም አቀፍ የጤና ኢኖቬሽንና ጥራት ጉባኤ "ኢኖቬሽን ለሁለንተናዊ የጤና ሽፋን" በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ሳህረላ አብዱላሂ፤ ኢትዮጵያ የኢኖቬሽን ጤና እንክብካቤ፣ የህሙማን ደህንነት፣ የጤና አገልግሎት ፍትሃዊነትና የጤና አመራርን ለማሳደግ መሰረት አድርጋ እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል።
በጤናው ዘርፍ ባለፉት ዓመታት በርካታ ለውጦች መመዝገባቸውን አስታውሰው፤ በህክምና ተቋማት የሚወልዱ እናቶች መጠን ከ80 በመቶ በላይ፣ የክትባት ሽፋን ከ90 በመቶ በላይ መድረሱንና ሌሎች የተመዘገቡ ውጤቶችን ለማሳያነት ዘርዝረዋል።
ኢትዮጵያ ብሔራዊ የዲጂታል ፍኖተ ካርታና የዲጂታል ጤና ስራ ክፍሎችን በማደራጀት ፈጠራን እንደ ስትራቴጂክ ችግር መፍቻ መቀበሏ ለተመዘገቡ ውጤቶች ዓይነተኛ ሚና ተጫውቷል ነው ያሉት።
በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በሚደገፉ መመርመሪያዎች፤ ቴሌሜዲስንና ሰው አልባ መሳሪያዎች በጤናው ዘርፍ ማህበረሰብን ለመድረስ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
በቀጣይም ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች፣ ወረርሽኝ፣ የጨቅላ ህጻናት ሞትንና ሌሎችን ለመቀነስ ፈጠራ የታከለበት አሰራርን በመዘርጋት ይበልጥ መስራት ይኖርብናል ብለዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ(ዶ/ር)፤ ፈጠራ የቅንጦት ጉዳይ ሳይሆን በጤናው ዘርፍ በጥራት፣ ፍትሃዊነትና የታካሚዎች ደህንነት ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመሙላት ያግዛል ብለዋል።
ጤና ሚኒስቴር ያዘጋጀውን ስትራቴጂ መሰረት በማድረግ ዘርፉን የሚያሸጋግሩ የፈጠራ ስራዎችን በትብብር እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ የዓለም ጤና ድርጅት ተወካይ ዶክተር ኦውን ካሉዋ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ሀገር በቀል የፈጠራ ውጤቶችን ተግባራዊ ማድረጓ ዘርፉን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር መሰረት ይሆናል ብለዋል።
የዓለም ጤና ስጋቶችን ተጽዕኖ የሚቋቋም የጤና ስርዓት ለመዘርጋት ፈጠራን ማዕከል ያደረጉ፣ ጥራትና ተደራሽነትን የሚያረጋግጡ አሰራሮችን መዘርጋት ወሳኝ መሆኑንም እንዲሁ።
የዓለም ጤና ድርጅት ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያን ብሔራዊ የጤና የፈጠራ ምህዳር ለማስፋት መደገፉን ጨምሮ በእናቶች ጤና አጠባበቅ ወባን በመቆጣጠር በዲጂታል ጤና አገልግሎት በቅርበት ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል።
ኢትዮጵያ ከነባራዊ ሁኔታዎች ጋር የተጣጣሙ ሀገር በቀል መፍትሔዎችን በፈጠራ በመደገፍ እያከናወነች ያለው ተግባር የጤናውን ዘርፍ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሻገር ቁልፍ ሚና እንዳለውም አመልክተዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት በጤና ዘርፍ ፈጠራንና ሌሎች የጤና መርሃ ግብሮች የሚተገበሩ አሰራሮችን በመደገፍ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር መስራቱን እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
ዓለም አቀፍ የጤና ኢኖቬሽንና ጥራት ጉባኤ ዛሬን ጨምሮ ለሶስት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን፤ በጤናው ዘርፍ የተሰሩ የፈጠራ ውጤቶችን የሚያሳይ አውደ ርዕይ ቀርቧል።
አዲስ አበባ፤ የካቲት 21/2017(ኢዜአ)፡- የምግብ ዋስትና እና ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ለነገ የሚተው የምርጫ ጉዳይ ባለመሆኑ በልዩ ትኩረት መረባረብ እንደሚገባ...
Feb 28, 2025
ሐረር፤ የካቲት 16/2017(ኢዜአ)፦ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ ሁሉን አቀፍ ስራዎች የህዝቡን ተጠቃሚነት ያሳደጉ መሆናቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ ጥር 30/2017(ኢዜአ)፦የየካቲት ወር የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ በጥር ወር በነበረበት የሚቀጥል መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስ...
Feb 8, 2025