የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ቁጥር ለማሳደግ እየተከናወነ ያለውን ስራ ማጠናከር ይገባል

Jun 27, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ሰኔ 19/2017(ኢዜአ) የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ቁጥር ለማሳደግ እየተከናወነ ያለውን ስራ ማጠናከር እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስገነዘበ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት በ40ኛ መደበኛ ስብሰባው የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የ2017 በጀት ዓመት የ11 ወራት የዕቅድ አፈፃጸም ሪፖርት አድምጧል።


የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) የሚኒስቴሩን የዕቅድ አፈፃጸም ሪፖርት ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።

ባለፉት 11 ወራት የኢኮኖሚ እድገትን የሚያፋጥን፣ ተደራሽ፣ የተቀናጀ፣ ቀልጣፋ እና ደህንነነቱ የተጠበቀ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ለመስጠት ሰፋፊ ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል።

ዘርፉ ለሀገር እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን በማንሳት፥ በህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት 960 ሚሊዮን ህዝብ ማጓጓዝ መቻሉን ተናግረዋል።


የአየር ትራንስፖርት የመንገደኛ አገልግሎትን ከማሻሻል አኳያ የሀገር ውስጥ የአየር ትራንስፖርት መዳረሻዎችን እና ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች በከፍተኛ መጠን ማደጋቸውን ገልጸዋል።

በሎጂስቲክስ ዘርፉም ደህንነቱ የተጠበቀ አገልግሎት በመስጠት ጠንካራ ውጤት መመዝገቡን ያነሱት ሚኒስትሩ፥ በወደቦች የነበረው የኮንቴነሮች ቆይታ ጊዜ በጉልህ መሻሻሉን አመላክተዋል።

የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው ዘርፉን ለማዘመን እና በቴክኖሎጂ ለመደገፍ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች አበረታች መሆናቸውን ገልጸዋል።

በህዝብ ትራንስፖርት መናኸሪያዎች ያለውን የተገልጋዮች እንግልት ለመቀነስ የቁጥጥር ስርዓቱ ውጤታማ ያልሆነበት ምክንያት ምንድን ነው? የሚል ጥያቄ አንስተዋል።

የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የሚመሩበት የአሰራር ስርዓት ስለመኖሩ እንዲሁም ተሽከርካሪዎቹ በቂ የኃይል መሙያ አላቸው ወይ? ሲሉም ነው የጠየቁት።

የትራፊክ አደጋን መቀነስ የሚያስችሉ ምን አይነት አዳዲስ ስትራቴጂዎች ተነድፈዋል፣ ህገወጥ ኬላዎች የንግድ ተወዳዳሪነትን እያወኩ በመሆኑ በዘላቂነት ለመፍታት ምን እየተሰራ ነው? ብለዋል።

ለጥያቄዎቹ ምላሽ የሰጡት የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሩ አለሙ ስሜ (ዶ/ር) በመናኸሪያዎች አካባቢ ያለውን ምቹ ያልሆነ ከባቢ እና ሌሎች ችግሮች ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም ሞዴል ሊሆኑ የሚችሉ መናኸሪያዎች መገንባታቸውን ገልጸው ከታሪፍ እና ትርፍ መጫን ጋር ያለው ችግር አሳሳቢ መሆኑን አንስተዋል።

ይህንንም ለመፍታት መንግስት ህግን እስከ ማሻሻል በርካታ እርምጃ መውሰዱን ገልጸው፤ ህግና ስርዓት እንዲከበር ህዝቡም ከተቆጣጣሪ አካላት ጋር በትብብር ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

አብዛኛው የትራፊክ አደጋዎች እየደረሱ ያሉት በአሽከርካሪ ስህተት መሆኑን እና ይህንን በመሰረታዊነት ለመፍታት በአዲስ መልክ የምዘና ስርዓት እንደሚከናወን ጠቁመዋል።

የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ገልጸው እነዚህ ተሽከርካሪዎች ኃይል የሚሞሉባቸው ቦታዎች በስፋት እየተገነቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የትራንስፖርት ፍሰቱን እንዲሁም ተወዳዳሪነትን የሚያቀጭጩ አሰራሮች እና ኬላዎች እንዲነሱ መደረጋቸውን ጠቁመው ኬላዎች ቢነሱም ሰዎች እየቆሙ ብር እንደሚቀበሉ ተናግረዋል።

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።


በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ መሰረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ መሐመድ አብዶ (ፕ/ር) የኢትዮ-ጅቡቲ ትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል የተሰራው ስራ ጠንካራ መሆኑን ገልጸዋል።


የበረራ ደህንነት አስተማማኝነት እና ዘርፉን ለማዘመን የለሙ ቴክኖሎጂዎች በጥንካሬ የሚወሰዱ መሆናችውን ጠቁመዋል።

ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የተሰጠው ትኩረት የሚደነቅ እና ሊሰፋ የሚገባው ነው ያሉት ሰብሳቢው፥ የኮንቴነሮች የወደብ ቆይታ አሁንም ሊሻሻል እንደሚገባ ነው አፅንኦት የሰጡት።

የትራፊክ አደጋዎችን በዘላቂነት ለመፍታት ቀጣይነት ያለው የአመለካከት ለውጥ የሚያመጡ የግንዛቤ ማስጨበጫዎችን መስጠት እንደሚገባ አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.