አዲስ አበባ፤ ሰኔ 20/2017 (ኢዜአ) የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በሁሉም አመልካቾች የሚጠበቅበትን ውጤቶች እያስመዘገበ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዠ ማሞ ምህረቱ ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምህረቱ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አፈጻጸም ጉዳዮችን አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በማብራሪያቸውም የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማስመዝገብ የሚያስችል አበረታች ሂደት ማስመዝገቡን አንስተዋል፡፡
የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ከተያዘለት የገቢ ማሳደግ፣ የዕዳ ሽግሽግ፣ የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚን ማምጣት፣ የውጪ ምንዛሪ ግኝት ማሳደግ ብሎም የፋይናንስ ዘርፉን ጤናማ ከማድረግ እንዲሁም ሌሎች ዓላማዎቹን ከማሳካት አኳያ አመርቂ ውጤቶች ማምጣቱን ተናግረዋል፡፡
የተሟላ ማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸሙ በውጤታማነት ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝ ያነሱት የባንኩ ገዥ፤ በወጭ ንግድ፣ በውጪ ምንዛሪ ክምችት፣ የዋጋ ንረትን በመቀነስ እንዲሁም በሌሎችም አመርቂ ውጤቶች እየታየበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ፕሮግራሙን ከሚደግፉት መካካል ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት ባወጣው ሪፖርት የኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም አፈጻጸም ከታቀደለት ግብ በላይ በመሳካት ላይ መሆኑን ማረጋገጡን ጠቁመዋል፡፡
የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊ ከተደረገ በኋላ የዋጋ ንረቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡
የምግብ ነክ የዋጋ ንረት ከ12 በመቶ በታች መሆኑን ያነሱት የባንኩ ገዥ፤ በሚቀጥለው ዓመት መጨረሻ ላይ አጠቃላይ የዋጋ ንረቱን ወደ ነጠላ አሃዝ ለማውረድ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ይህንንም ለማሳካት ጥብቅ የሆነ የገንዘብና የፊሲካል ፖሊሲ ይወሰዳል ያሉት የባንኩ ገዥ፤ ምርታማነትን ማሳደግ፣ እሴት በመጨመር የንግድ ስርዓቱን ማሳለጥ እና ሌሎች እርምጃዎች እንደሚወሰዱም ጠቁመዋል፡፡
በተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በውጪ ምንዛሪ ስርዓት ውስጥ የተወሰደው እርምጃ ስርነቀልና ተመኑን በገበያ ከመወሰን ባለፈ በአጠቃላይ የውጪ ምንዛሪ ስርዓቱ የተሻለ እንዲሆን መደረጉን ተናግረዋል፡፡
በዚህም በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በማምጣት ላይ የሚገኘው ውጭ ምንዛሪ ፍሰት መጨመሩን አንስተው፤ ባለፉት 11 ወራት የወጭ ንግድ አፈጻጸም ማደጉን ገልጸዋል፡፡
ከውጭ ምንዛሪ ሪፎርሙ በፊት የአገሪቷ የወጭ ንግድ ሦስት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ዶላር እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ላይ ይህ ዓመት በሚጠናቀቅበት ጊዜ የወጪ ንግድ ስምንት ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ ጠቁመዋል፡፡
የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የታቀደለትን ግቦች በማሳካት ላይ የሚገኘው በቂ ዝግጅትና ጥናቶች ተደርገው ወደ ስራ በመግባቱ መሆኑን አንስተው፤ ሪፎርሙ በርካታ ጉዳዮችን አሰባስቦ መተግበሩም ለውጤታማነት ማብቃቱን ተናግረዋል፡፡
ማሻሻያው ኢንቨስትመንትን ከመሳብ ረገድ ትልቅ ውጤት እያስገኘ መሆኑን ጠቁመው፤ በቀጣይም የተገኙ ስኬቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠል በትኩረት እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡
የውጭ ምንዛሪ ተመን በገበያ እንዲወሰን ከማድረግ ጎን ለጎን የፊሲካል ፖሊሲና አዲስ የገንዘብ ፖሊሲዎችን እንዲሁም ኢንቨስትመንትን የሚያበረታቱ የተለያዩ የህግ ማሻሻያዎች ተግባራዊ መደረጋቸው ከፍተኛ ውጤት እንዲመዘገብ ማስቻላቸውን ተናግረዋል፡፡
አዲስ አበባ፤ የካቲት 21/2017(ኢዜአ)፡- የምግብ ዋስትና እና ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ለነገ የሚተው የምርጫ ጉዳይ ባለመሆኑ በልዩ ትኩረት መረባረብ እንደሚገባ...
Feb 28, 2025
ሐረር፤ የካቲት 16/2017(ኢዜአ)፦ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ ሁሉን አቀፍ ስራዎች የህዝቡን ተጠቃሚነት ያሳደጉ መሆናቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ ጥር 30/2017(ኢዜአ)፦የየካቲት ወር የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ በጥር ወር በነበረበት የሚቀጥል መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስ...
Feb 8, 2025