የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በዝናብ አጠር አካባቢዎች የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል የዕቀባ እርሻን የማስፋፋት ተግባር እየተከናወነ ነው

Jul 1, 2025

IDOPRESS

በና-ፀማይ፤ሰኔ 23/2017(ኢዜአ)፦ በዝናብ አጠር አካባቢዎች የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል የዕቀባ እርሻን በማስፋፋት የመሬት ለምነትንና የውሃ ትነትን ለመቀነስ እየተሰራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ገለጸ።

በደቡብ ኦሞ ዞን በና-ፀማይ ወረዳ በጎልዲያ ቀበሌ በዕቀባ እርሻ የተከናወነ የግብርና ልማት የመስክ ምልከታና የልምድ ልውውጥ መረሃ ግብር ተካሄዷል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ እና የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አድማሱ አወቀ በወቅቱ እንዳሉት የዕቀባ እርሻ (Conservation Agriculture) ዝናብ አጠር በሆኑ አካባቢዎች ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ሚናው የጎላ ነው።


ሰብሎችን አፈራርቆ በመዝራት፣ የሰብል ተረፈ-ምርቶችን በመጎዝጎዝ የውሃ ትነትን ለመቀነስ እና የውሃ ስርገትን በመጨመር የሚከናወነው የዕቀባ እርሻ ተግባር ምርታማነትን ለመጨመር ያስችላል ብለዋል።

የግብርና ቴክኖሎጂው የግሪን ሀውስ ጋዞችን በመቀነስ የአየር ብክለትን ለመከላከልና የአፈር አሲዳማነትንም በመቀነስ ለምነትን ማሻሻል የሚያስችል ምርታማነት እንዲጠመር ያግዛል ሲሉ ገልፀዋል።

በቀጣይም ቴክኖሎጂውን በክልሉ በተመረጡ አካባቢዎች የማላመድና የማስፋፋት ስራ እንደሚሰራም አመላክተዋል ።

የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማዕከል ማሊኮ በበኩላቸው ቴክኖሎጂው የአርብቶ አደሩን የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተጀመሩ የግብርና ልማት ስራዎችን ውጤታማ ያደርጋል ብለዋል።


የኃይለማርያም እና ሮማን ፋውንዴሽን የዕቀባ እርሻን በበና-ፀማይ ወረዳ ለማስፋፋት ያደረገው ተግባር በዞኑ በሁሉም አካባቢዎች ለማላመድ እንደሚሰራም ተናግረዋል።

የኃይለማርያም እና ሮማን ፋውንዴሽን ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ ሶስና ኃይለማርያም (ዶ/ር) በበኩላቸው በደቡብ ኦሞ ዞን ሐመር እና በና- ፀማይ ወረዳዎች በ40 አርሶ አደር እና አርብቶ አደር ማሳዎች ላይ ቴክኖሎጂውን የማላመድ ስራ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል ።


በፋውንዴሸኑ የግብርና ትራንስፎርሜሽን፣ የምግብና ሥነ-ምግብ ዋስትና ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ ፈላሀ በበኩላቸው፥ ቴክኖሎጂው የአፈር መሸርሸርን በመከላከል በአፈር ውስጥ ያሉ ንጥረ-ነገሮችን ለመጠበቅ ያስችላል ብለዋል።

በተለይ የአየር ንብረት ለውጡን ተከትሎ የሚመጣውን ጫና ለመከላከል ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ እንደ ደቡብ ኦሞ ዞን ላሉ ዝናብ አጠር ቆላማ አካባቢዎች ተስማሚና ተመራጭ መሆኑን አረጋግጠዋል ።


የበና-ፀማይ ወረዳ የጎልዲያ ቀበሌ አርሶ አደር ኤርሚያስ አድነው፥ በፋውንዴሽኑ እና በግብርና ባለሙያዎች ምክረ-ሀሳብ መሰረት ቴክኖሎጂውን በማሳቸው ላይ ተግባራዊ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ተናግረዋል ።


ይህም የበቆሎ ሰብላቸውን ምርታማነት በማሳደግ፣ አረምን በመቆጣጠርና የሰብል እድገትን በማፋጠን ምርታማነታቸው እንዲጨምር ማድረጉን አንስተዋል።

ሌላው አስተያየት ሰጪ አርሶ አደር ማቲዮስ ገርሾ በበኩላቸው ቴክኖሎጂው ቀደም ሲል በማሳቸው አጋጥሞ የነበረውን የአፈር ለምነት የመቀነስ ችግር የፈታ መሆኑን ገልፀዋል።


እንደ አርሶ አደሩ ገለፃ የሚያገኙትን ጥቂት ምርት የእቀባ እርሻን ተግባራዊ በማድረጋቸው ምርታማነታቸው ጨምሯል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.