የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በክልሉ የሻይ ልማትን በማስፋፋት ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት አበረታች ናቸው - ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር ኢ/ር)

Jul 3, 2025

IDOPRESS

ቦንጋ፤ ሰኔ 25/2017(ኢዜአ)፦ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የሻይ ልማትን በማስፋፋት ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት አበረታች መሆናቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር ኢ/ር) ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በቦንጋ ከተማ አስተዳደር የሚገኘውን የዲንቻ የሻይ ችግኝ ጣቢያ ተመልክተዋል።

የሻይ ልማት ችግኝ ጣቢያው በክልሉ የሻይ ልማትን ለማስፋፋት የሻይ ችግኝ ከሚዘጋጅባቸው ጣቢያዎች በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው።

በምልከታው ርዕሰ መስተዳድሩ ችግኞችን በአግባቡ አፍልቶ ተደራሽ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት የሚበረታቱና መጠናከር ያለባቸው መሆኑን ገልጸው፣ አርሶ አደሩ በሻይ ልማት በስፋት ተሰማርቶ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆን የክልሉ መንግስት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል።


የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ሀላፊ ማስረሻ በላቸው በክልሉ የሻይ ልማትን ለማስፋት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በልማቱ የአርሶ አደሩን የልማት ተሳትፎ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ገልፀው፣ ባለሀብቶችን በመጋበዝ ፋብሪካ እንዲያቋቁሙ ለማድረግም እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል።

የካፋ ዞን ግብርና፣ አካባቢ ጥበቃና ህብረት ሥራ ልማት መምሪያ ሀላፊ ጋዎ አባመጫ በበኩላቸው፣ በፕሮጀክትና በተደራጁ አርሶ አደሮች ብቻ ለበርካታ ዓመታት ተወስኖ የቆየውን የሻይ ልማት ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

በዚህም በአራት ወረዳዎች የችግኝ ጣቢያዎችን በማቋቋምና ለቀጣይ ዓመት ተከላ የሚሆን ከ1 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለማዘጋጀት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

ከዚህ ቀደም የሻይ ልማት ከሚካከናወንባቸው 7 ቀበሌዎች በተጨማሪ 22 ቀበሌዎች ላይ ልማቱን ለማስፋት የሚሳተፉ አርሶ አደሮችና የመሬት ልየታ ሥራ ትኩረት ተሰጥቶ እየተከናወነ መሆኑንም ገልፀዋል።


ይህም ከዚህ ቀደም በአንድ አካባቢ ብቻ ተወስኖ የቆየውን ልማት ለማስፋትና በዘርፉ የሚሰማሩ የአርሶ አደር ማህበራትን ቁጥር ለማሳደግ ይረዳል ብለዋል።

በተጨማሪም ወደ ዩኒየን ደረጃ በማሳደግ የገበያ ችግርን ለመፍታትና እሴት ጨምሮ ምርቱን ለገበያ ለማቅረብ ዕድል ይፈጥራል ነው ያሉት።

በዲንቻ የሻይ ልማት ችግኝ ጣቢያ ጉብኝት ላይ የክልልና የዞን ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.