አዳማ፤ ሰኔ 25/2017 (ኢዜአ)፦ በበጀት ዓመቱ ህብረተሰቡን እና ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ የከተሞችን እድገት ለማፋጠን በተከናወኑ ተግባራት ውጤት መገኘቱን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ አስታወቁ።
ሚኒስቴሩ የ2017 በጀት አመት የስራ አፈፃፀምና የ2018 ዕቅድ ከባለድርሻ አካላት ጋር በአዳማ እየገመገመ ነው።
መድረኩ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ፣ የአገሪቱ ከተሞች ባለፉት ጥቂት ዓመታት እያደጉና ለህብረተሰቡ የሚያስገኙት ጥቅም ከፍ እያለ መጥቷል።
በበጀት ዓመቱ የከተሞችን እድገት ለማፋጠንና ለህብረተሰቡ የሚሰጡ የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ስራዎችን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል።
በተለይም በበጀት ዓመቱ የከተሞችን እድገት ለማፋጠን ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰው በዚህም የከተሞች ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶችን ቀልጣፋ በማድረግ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለማስወገድ በተከናወኑ ተግባራት አበረታች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በመኖሪያ ቤቶች ግንባታ፣ በከተማ ግብርና፣ በከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት እንዲሁም በካዳስተር ትግበራ ውጤታማ ስራ መከናወኑን አስረድተዋል።
ከተሞችን ለኑሮ ምቹና ሳቢ ከማድረግ ባለፈ የከተሞችን ገቢ ለማሳደግ የማዘጋጃ ቤት አገልግሎትን ለማዘመን፣ የከተሞች መሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን በማስፋፋት ረገድ በርካታ ውጤቶች መገኘታቸውንም አስረድተዋል።
የከተሞች የምግብ ዋስትና መርሃ ግብርም የበርካታ ዜጎችን ህይወት በመቀየር የሥራና የቁጠባ ባህልን ማጎልበት መቻሉን ሚኒስትሯ ተናግረዋል።
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር አማካሪ አቶ ተስፋዬ ሀይለሚካኤል በመድረኩ ላይ ባቀረቡት ሪፖርት እንዳመለከቱት በከተሞች በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል በከተማ በምግብ ዋስትና መርሃ ግብር 15 ቢሊዮን ብር ስራ ላይ መዋሉን አመልክተዋል።
በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎችን በተሰማሩበት የምግብ ዋስትና መርሃ ግብር ከእለት ገቢያቸው 770 ሚሊዮን ብር በመቆጠብ ወደ ሌላ የልማት ስራ መሸጋገራቸውን ጠቁመዋል።
የማዘጋጃቤታዊ ገቢ ለማሳደግ በተደረገ ጥረት 76 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን ገልጸው አፈፃፀሙ ከአምና ጋር ሲነፃፀር በ30 ቢሊዮን ብር ብልጫ ማሳየቱን አብራርተዋል።
በከተሞች ማዘጋጃቤታዊ አገልግሎት የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ፣ የአረንጓዴ ልማትና በመንገድ መሰረተ ልማት አቅርቦት ላይ መሻሻል መታየቱን ጠቅሰዋል።
በመድረኩ ላይ የሚኒስቴሩ ተጠሪ ተቋማት እንዲሁም ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ነው።
አዲስ አበባ፤ የካቲት 21/2017(ኢዜአ)፡- የምግብ ዋስትና እና ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ለነገ የሚተው የምርጫ ጉዳይ ባለመሆኑ በልዩ ትኩረት መረባረብ እንደሚገባ...
Feb 28, 2025
ሐረር፤ የካቲት 16/2017(ኢዜአ)፦ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ ሁሉን አቀፍ ስራዎች የህዝቡን ተጠቃሚነት ያሳደጉ መሆናቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ ጥር 30/2017(ኢዜአ)፦የየካቲት ወር የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ በጥር ወር በነበረበት የሚቀጥል መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስ...
Feb 8, 2025