የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

የአካባቢን ሀብት ለይቶ ጠንክሮ መስራት ከተቻለ ውጤታማ መሆን ይቻላል--የሳላማጎ ወረዳ ወጣቶች

Jul 3, 2025

IDOPRESS

ድሜ-ገሮ፤ ሰኔ 25/2017 (ኢዜአ)- የአካባቢን ሀብት ለይቶ ጠንክሮ መስራት ከተቻለ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል በደቡብ ኦሞ ዞን ሳላማጎ ወረዳ በግብርና ስኬት እያስመዘገቡ ያሉ ወጣቶች ገለጹ።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት ወጣቶቹ ፣ የአካባቢያቸውን ፀጋ ለማልማት ተግተው በመስራታቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤት እያስመዘገቡ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

በሳላማጎ ወረዳ የድሜ ገሮ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት አለሙ ላስታ እንደገለጸው ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ ካገለገለበት የሀገር መከላከያ ሠራዊት በ2001 በክብር ተሰናብቶ ወደግብርና ልማት ገብቷል።

በሀገር መከላከያ ሠራዊት ቆይታው ኢትዮጵያን ተዘዋውሮ የመመልከት ዕድል ማግኘቱን የተናገረው ወጣቱ፣ ይህም ለእርሻ ምቹ ያልሆኑ መሬቶችን ጭምር በማልማት እንዴት ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻል ተሞክሮ ለማግኘት እንዳስቻለው ተናግሯል።

ለእርሻ ምቹ ያልሆኑ መሬቶችን ጭምር ማልማት ከተቻለ አካባቢው ያለው ለም መሬት ለምን ጦሙን ያድራል በሚል ቁጭት ቀዳሚ ትኩረትን ያደረገው ለዓመታት ሳይታረስ የቆየውን የቤተሰቡን 5 ሄክታር መሬት ማልማት ነበር።


የወጣቱን የሥራ ተነሳሽነትና ጥረት የተመለከቱት የሳላማጎ ወረዳ እና የደቡብ ኦሞ ዞን አስተዳደር 20 ሄክታር የእርሻ መሬት ድጋፍ በማድረጋቸው በአሁኑ ወቅት በ25 ሄክታር መሬት ላይ ሩዝ፣ ማሾ፣ በቆሎና ካሳቫ እያመረተ መሆኑን ተናግሯል።

በአካባቢ ያለን ጸጋ በማልማትና ጠንክሮ በመስራት ውጤት ማስመዝገብ ይቻላል ያለው ወጣት አለሙ በአሁኑ ወቅት በግብርና ልማት ሥራው ለ25 ሰዎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል።

እንደ ወጣት አለሙ ሁሉ በግብርና ሥራ በመሰማራት ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን የገለጸው ሌላው በወረዳው የዲሜ ገሮው ቀበሌ ወጣት ደርግሰው ማንታራዤ ነው።

ቀደም ሲል ሲተዳደርበት በነበረው የሹፍርና ሙያ ለ6 ዓመታት ቢሰራም በኑሮው ላይ የሚፈልገውን ለውጥ ለማምጣት አልቻለም።


የእርሻ ሥራ ቢጀምር ውጤታማ እንደሚሆን ከቅርብ ወዳጆቹ በቀረበለት ምክረ ሀሳብ መሰረት የግብርና ባለሞያዎችን በማማከር የግብርና ልማቱን እንደጀመረ ያስታውሳል።

"በመንግስት ድጋፍና በግብርና ባለሙያዎች እገዛ በሁለት ሄክታር መሬት ላይ ለሙከራ የሚሆን ካሳቫ አመረትኩ'' የሚለው ወጣቱ፣ በመጀመሪያው ዙር ብቻ ከምርቱ ሽያጭ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በማግኘት ስኬታማ መሆኑን ተናግሯል።

''የኔን ፈለግ በመከተል በርካታ ወጣቶች ወደ እርሻ ስራው እየተሰማሩ ነው'' የሚለው ወጣቱ፣ ለበርካታ ወጣቶች አርአያ በመሆኑ ደስተኛ መሆኑን ነው የተናገረው።

የእርሻ ሥራ ውጤታማነቱን በማረጋገጥ በአሁኑ ወቅት የካሳቫ ልማትን በ12 ሄክታር መሬት ላይ እያከናወነ ይገኛል።

ከእዚህም 3 ሺህ 600 ኩንታል በላይ ምርት በማምረት ከሽያጩ ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ እንደሚጠበቅ ተናግሯል።

በቀጣይም የተለያዩ የቅባት እህሎችን በማልማትም ለማዕከላዊ ገበያ የማቅረብ ዕቅድ እንዳለው የሚናገረው ወጣት ደርግሰው፥ ለዚህ አገልግሎት እንዲውልም የጭነት ተሽከርካሪ ለመግዛት ማቀዱን ተናግሯል።

ወረዳው በግብርና ልማት ሰፊ አቅም እንዳለው የገለጹት ደግሞ የሳላማጎ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቶማስ አስካም ናቸው።


እንደእሳቸው ገለጻ የአካባቢው ወጣቶች በግብርና ልማት ተሰማርተው ሀብት እንዲያፈሩ ጥረት እየተደረገ ነው።

በግብርና ልማት ለተሰማሩ ወጣቶች ከክህሎት ድጋፍ ባሻገር የአፈር ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን ጠቅሰው፣ ወጣቶቹ በስፋት እንዲያለሙም የእርሻ ትራክተር ድጋፍ በማድረግ እገዛ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.