የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በሲዳማ ክልል በአምራች ኢንዱስትሪው ላይ የታየውን መነቃቃት ለማስቀጠል ቅንጅታዊ አሰራር ተዘርግቷል

Sep 30, 2025

IDOPRESS

🔇Unmute

ሀዋሳ፤ መስከረም 19/2018 (ኢዜአ)፦ በሲዳማ ክልል በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በአምራች ኢንዱስትሪው ላይ የታየውን መነቃቃት ለማስቀጠል ቅንጅታዊ አሰራር መዘርጋቱ ተገለጸ።

የሲዳማ ክልል የኢንዱስትሪ ልማት ምክር ቤት በክልሉ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ እየተመዘገበ ያለውን ውጤት በማስፋት የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መክሯል።


በመድረኩ ላይ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የትምህርት ቢሮ ሃላፊና የምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ በየነ በራሳ የአምራች ኢንዱስትሪውን ማነቆዎች ለመፍታት የጋራ ምክር ቤቱ ከፍተኛ ድርሻ ማበርከቱን ተናግረዋል።

በተለይም በፋይናንስና፣ በሀይል አቅርቦትና በጥሬ ዕቃ እጥረት ላይ ሲገጥሙ የነበሩ ችግሮችን በመፍታት በኩል የጋራ ምክር ቤቱ እገዛ የማይተካ እንደነበረ ገልጸዋል።

ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የሚደረገው ድጋፍ እንደ ሀገር ከተተገበረው የኢትዮጵያ ታምርት ሀገራዊ ንቅናቄ ጋር በመቀናጀቱ ለስኬቱ አይነተኛ ድርሻ ማበርከቱንም አክለዋል።

በኢንዱስትሪው ላይ የታየውን መነቃቃት ለማጠናከር የክልሉ መንግስት በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከዚህ በተጓዳኝ የኢንቨስትመንት መሬት ወስደው በገቡት ውል መሰረት ያላለሙት ላይ እርምጃ መውሰዱን ተናግረዋል።

ቀደም ሲል በክልሉ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት መጓደል አምራች ኢንዱስትሪዎች ውጤታማ እንዳይሆኑ ማድረጉንና በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ችግሩ መፈታቱን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ጎሳዬ ጎዳና ናቸው።



ይህም የአምራች ኢንዱስትሪዎች አቅምን በማሳደግ የወጪና ተኪ ምርቶች ምርት እየጨመረ እንዲመጣ ማድረጉን አስረድተዋል።

ንቅናቄው የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ቁጥር ከ700 ወደ 1 ሺህ 450 በላይ እንዲያድግ ማስቻሉንም አቶ ጎሳዬ ተናግረዋል።

ለአብነትም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ ያለችው ተኪ ምርቶችን ለማምረት መቻሉን ተናግረዋል።

በማዕከላዊ ገበያ በኩል ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶችም ከ51 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን ገልጸው፣ ኢንዱስትሪዎቹ ከ18 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውንም ተናግረዋል።

በዘርፉ እየታየ ያለውን መነቃቃት የበለጠ ለማስፋትና ልምዶችን ለመቀመር እንዲሁም አዳጊ ፍለጎቶችን ተደራሽ ለማድረግ ባለድርሻዎች ሚናቸውን አጠናክረው ማስቀጠል የመድረኩም ዓላማ መሆኑን አቶ ጎሳዬ አክለዋል።


ከባለድርሻ አካለት መካከል አስተያየታቸውን የሰጡት በኢትዮጵያ ልማት ባንክ የሀዋሳ ዲስትሪክት ሥራ አስኪያጅ አቶ ተሾመ ጌታነህ በበኩላቸው ከኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ወዲህ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ከፍተኛ መነቃቃት እየታየ ነው ብለዋል።

ዘርፉን ለማነቃቃት በተዘረጋው ቅንጅታዊ ስራ ባንኩ የበኩሉን እየተወጣ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በምክክር መድረኩ ላይ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ ብድር አቅራቢ ባንኮችን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻዎችም ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.