የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

ኢጋድ እና ጀርመን በፍልሰት አስተዳደር እና አየር ንብረት ለውጥ መከላከል ያላቸውን ስትራቴጂካዊ አጋርነት እንደሚያጠናክሩ ገለጹ

Oct 11, 2025

IDOPRESS

🔇Unmute

አዲስ አበባ፤ መስከረም 30/2018 (ኢዜአ)፦ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) እና ጀርመን በፍልሰት አስተዳደር እና አየር ንብረት ለውጥ መከላከል ያላቸውን የቆየ ስትራቴጂካዊ አጋርነት የበለጠ ለማጎልበት እንደሚሰሩ አስታወቁ።

ጀርመን ለኢጋድ ቀጣና የተለያዩ የፋይናንስ ድጋፍ ማዕቀፎችንም ይፋ አድርጋለች።

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) እና ጀርመን በልማት ትብብራቸው ዙሪያ በጅቡቲ ስትራቴጂካዊ ምክክር አድርገዋል።


በምክክሩ ላይ የኢጋድ ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር)፣ የጀርመን የኢኮኖሚ ትብብር እና ልማት ሚኒስቴር የምስራቅ አፍሪካ ዘርፍ ኃላፊ ሃኒንግ እና በጅቡቲ የጀርመን አምባሳደር ሄይከ ፉለር (ዶ/ር) ተገኝተዋል።

ስትራቴጂካዊ ምክክሩ ሁለቱ ወገኖች በአፍሪካ ቀንድ ባሉ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ትብብር የገመገሙ ሲሆን በቀጣይ የግንኙነት ማዕቀፎች ላይም መክረዋል።

ፍልሰት እና አየር ንብረት ለውጥ የውይይቱ አበይት ማጠንጠኛዎች ናቸው።

ሁለቱ ወገኖች የጀርመን ቀጣናዊ የፍልሰት ፈንድ ዳግም ማዋቀር ሂደት መልካም ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በማንሳት የኢጋድ የቀጣናዊ የፍልሰት ፖሊሲ ማዕቀፍ ፣ የነጻ እንቅስቃሴ የህግ ማዕቀፎች እና የዜጎችን የአኗኗር ሁኔታ የማጠናከር ስራ ለመደገፍ የጋራ ስምምነት ላይ ተደርሷል።

ጀርመን ለኢጋድ የፍልሰት ፖሊሲ ትግበራ ፕሮጀክት ቀጣይ ምዕራፍ ትግበራ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዩሮ ለመደገፍ ቃል መግባቷን ኢዜአ ከቀጣናዊ ተቋሙ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

በተጨማሪም ጀርመን በኢጋድ አባል ሀገራት ለሚከናወኑ የማይበገር የአየር ንብረት ለውጥ አቅም ግንባታ ስራዎች በቀጣናዊ የአደጋ ፋይናንስ ፕሮግራም አማካኝነት 22 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዩሮ ለመደገፍ መዘጋጀቷ ተመላክቷል።

የፋይናንስ ማዕቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ ድንገተኛ አደጋዎችን የመከላከል ስራዎች የሚደገፍ እና የኢጋድ የድርቅ አደጋን የመቋቋም እና ዘላቂነት ኢኒሼቲቭ ጨምሮ ሌሎች ፕሮጀክቶችን የሚደግፍ ነው።

በስትራቴጂካዊ ምክክሩ ሁለቱ ወገኖች ውጤት ተኮር፣ አሳታፊ እና ተጠያቂነትን መሰረት ያደረገ አጋርነትን መፍጠር እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ኢጋድ እና ጀርመን ትብብራቸውን ለማጠናከር፣ የጋራ ስራዎቻቸው የአባል ሀገራት የቅድሚያ ትኩረቶች ያማከሉ እንዲሆኑና የፖሊሲ ምክክራቸውን በመደበኛነት ለማከናወን ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።

ኢጋድ እና ጀርመን 37 ዓመታትን ያስቆጠረ አጋርነት እንዳላቸው መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.