የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በዞኑ በድርቅ ሊከሰት የሚችለውን የምግብ እህል እጥረት ችግር ለመፍታት ከ24 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት እየተሰራ ነው

Oct 11, 2025

IDOPRESS

🔇Unmute

ነገሌ ቦረና ፤ መስከረም 30/2018 (ኢዜአ)፡-በምስራቅ ቦረና ዞን በድርቅ ምክንያት የሚከሰትን የምግብ እህል እጥረት ችግር ለመፍታት ከ24 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት ታቅዶ ወደስራ መገባቱን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ገለጸ።

በጽህፈት ቤቱ የሰብል ልማትና ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ ሊበን ቦሩ እንደገለጹት፣ በምስራቅ ቦረና ዞን በተደጋጋሚ በሚከሰት ድርቅ ምክንያት የምግብ እህልና የእንስሳት መኖ እጥረት ችግር ይከሰታል።

ችግሩን ለመቋቋም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት መጀመሩንና ይህም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የስንዴ ተረፈ ምርቱንም ለእንስሳት መኖ ለማዋል እያስቻለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


ዘንድሮም በዞኑ ከዘጠኝ ወረዳዎች ውስጥ በስድስቱ የመስኖ ልማት በማከናወን የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት ከታቀደው 24 ሺህ 793 ሄክታር መሬት 856 ሺህ 633 ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱንም አቶ ሊበን አስረድተዋል፡፡

ዘንድሮ በዞኑ በበጋ መስኖ ለማልማት የታቀደው መሬት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ4ሺህ 787 ሄክታር ብልጫ አለው ብለዋል።

በጽህፈት ቤቱ የመካናይዜሽን ምርት ግብአት አጠቃቀም ቡድን መሪ አቶ ገመዳ ሀሰን ለመስኖ ልማቱ ከ4ሺህ ኩንታል በላይ የስንዴ ምርጥ ዘርና ከ27 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለአርብቶ አደሩ መከፋፈሉን ገልጸዋል፡፡

በዞኑ ሊበን ወረዳ የጎቢቻ ቀበሌ ነዋሪ ሀጂ ኢብራሂም ጡና በመስኖ ልማቱ ከተሳተፉ አርብቶ አደሮች መካከል አንዱ ናቸው፡፡


ሰፊ መሬት ቢኖረንም አካባቢያችን ዝናብ አጠር በመሆኑ ለበርካታ ዓመታት በእንስሳት እርባታ ሥራ ላይ ብቻ አሳልፈናል ብለዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በበጋ ወራት የጀመሩት የመስኖ ስንዴ ልማት ከራሳቸው ባለፈ ምርቱን ለገበያ በማቅረብ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እያደረጋቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተያዘው ዓመትም ሁለት ሄክታር ተኩል መሬታቸውን በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት አቅደው ወደተግባር መግባታቸውን አስረድተዋል፡፡

በምስራቅ ቦረና ዞን ቆላማ ወረዳዎች ከመስከረም አጋማሽ እስከ ጥቅምት ወር የመኸር ዝናብ የሚጥልበት ወቅት ሲሆን ከዚህ ጎን ለጎን እስከ ታህሳስ ወር የሚዘልቅ የበጋ መስኖ ልማት እንደሚካሄድ ከዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.