የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

የንጋት ሐይቅ የተቀናጀ ማስተር ፕላን ዝግጅት የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ትሩፋቶችን በሚገባ መምራት የሚያስችል ነው

Oct 15, 2025

IDOPRESS

🔇Unmute

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 4/2018(ኢዜአ)፦ የንጋት ሐይቅ የተቀናጀ አስተዳደርና አጠቃቀም ማስተር ፕላን ዝግጅት የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ትሩፋቶችን በሚገባ መምራት የሚያስችል መሆኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውሃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢና የአካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አወቀ አምዛዬ(ዶ/ር) ገለጹ።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር) በበኩላቸው የኢትዮጵያን የዘመናት ፍትሐዊ የውሃ ሃብት የመጠቀም መብት በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ስኬት ማረጋገጥ እንደተቻለ ገልጸዋል።


የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ - የንጋት ሐይቅ የረቂቅ ማስተር ፕላን ጥናት ማስጀመሪያ የምክክር መድረክ በቢሾፍቱ ከተማ ተካሂዷል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውሃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢና የአካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አወቀ አምዛዬ(ዶ/ር)፤ የንጋት ሐይቅ የተቀናጀ አስተዳደርና አጠቃቀም ማስተር ፕላን ዝግጅት የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ትሩፋቶችን በሚገባ መምራት የሚያስችል ነው ብለዋል።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ከሚያመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል ባለፈ በዓሳ ሃብት፣ ቱሪዝምና ትራንስፖርት መስክ የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ በዕቅድ መምራት እንደሚኖርባቸው አስገንዝበዋል።

ምክር ቤቱም የንጋት ሰው ሰራሽ ሐይቅን ጨምሮ የዓባይ የውሃ ተፋሰስ ደኅንነትን የሚያስጠብቁ የህግ፣ የፖሊሲ ማዕቀፍ ዝግጅት ጉዳዮች ላይ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል።


የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር)፤ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግደብ መመረቅ የዜጎች ትልቅ የኩራት ምንጭ መሆን መቻሉን ገልጸዋል።

በዚህም የኢትዮጵያን የዘመናት ፍትሐዊ የውሃ ሃብት የመጠቀም መብት በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ስኬት አረጋግጠናል ብለዋል።

ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዜጎች የዘመናት በውሃ ሃብታቸው የመጠቀም ቁጭትን በተባበረ ክንድ ምላሽ በመስጠት ዘርፈ ብዙ ትሩፋት ማግኘት የቻሉበት መሆኑን ተናግረዋል።

የግድቡ የኃይል አቅርቦትም ከሀገር ባሻገር ቀጣናዊ የትስስር አቅምን በማሳደግ ትልቅ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እየፈጠረ እንደሚገኝ አንስተዋል።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የፈጠረውን የንጋት ሰው ሰራሽ ሐይቅ ዘርፈ ብዙ ትሩፋት በሥርዓት ማስተዳደር የሚያስችል ማስተር ፕላን እየተዘጋጀ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።


የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጌታሁን አብዲሳ፤ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ በኢትዮጵያውያን አንጡራ ሀብት የተገነባ የማድረግ አቅማችንና የአንድነታችን መገለጫ ነው ብለዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከሚሰጠው የኃይል አቅርቦት ባሻገር የንጋት ሐይቅ ለኢትዮጵያውያን ዘርፈ ብዙ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ጸጋዎችን ይዞ መምጣቱን ገልጸዋል።

የንጋት ሐይቅና የአካባቢው አስተዳደር ማስተር ፕላን ዝግጅትም ሐይቁ የፈጠራቸውን ጸጋዎች በተቀናጀ ሥርዓት ለማስተዳደር ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው መሆኑን ተናግረዋል።

በንጋት ሐይቅ የረቂቅ ማስተር ፕላን ጥናት ማስጀመሪያ የምክክር መድረክ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.