የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ለግብርና እና ለእንስሳት የመጠጥ ውሃ አገልግሎት የሚውል የመስኖ ፕሮጀክት ግንባታ ተጀመረ

Oct 23, 2025

IDOPRESS

🔇Unmute

ጭሮ ፤ጥቅምት 12/2018(ኢዜአ)፡- በምዕራብ ሐረርጌ ዞን በዳሮ ለቡ ወረዳ 140 ሚሊዮን ብር ለግብርና እና ለእንስሳት መጠጥ ውሃ አገልግሎት የሚውል መለስተኛ መስኖ ፕሮጀክት ግንባታ መጀመሩን የዞኑ መስኖና አርብቶ አደር ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

በዞኑ እስካሁን ግንባታቸው ተጠናቆ ስራ የጀመሩ የመስኖ ፕሮጀክቶች ከአራት ሺህ በላይ ለሚሆኑ የቤተሰብ መሪዎች አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ተናግረዋል።

በጽህፈት ቤቱ የግንባታ ኮንትራት አስተዳደር ቁጥጥር ቡድን መሪ አቶ አብዲ መሀመድ እንዳሉት በዚህ ዓመት ግንባታው የተጀመረው የዳሮ ለቡ ወረዳ የመስኖ ፕሮጀክት ለግብርና እና ለእንስሳት የመጠጥ ውሀ አገልግሎት የሚውል መለስተኛ የውሀ ግድብ ነው፡፡

በዚህ ወር የተጀመረው የመስኖ ፕሮጀክቱን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በማጠናቀቅ አገልግሎት እንዲሰጥ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምርም በወረዳው ለሚገኙ ከ700 በላይ ለሚሆኑ የቤተሰብ መሪዎች፣ ለአርብቶ እና አርሶ አደሮች አገልግሎት መስጠት እንደሚችል አመልክተዋል፡፡

በተጨማሪም ከ160 ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ በማልማት ለግብርና ልማቱ መስፋፋት አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም አስረድተዋል፡፡

በዞኑ ጉምቢ ቦርዶዴ እና ቡርቃ ዲምቱ ወረዳዎች ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ከተጀመሩ አራት የመስኖ ፕሮጀክቶች ሶስቱ ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውንም ተናግረዋል፡፡

የመስኖ ፕሮጀክቶቹ በወረዳዎቹ የሚገኙ ከአራት ሺህ በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ ማድረጋቸውን አመልክተዋል፡፡

በጉምቢ ቦርዶዴ ወረዳ የተገነቡት የጎሎልቻና ኬንተሪ የመስኖ ግድቦች ከ2 ሺህ 300 ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ማልማት የሚችሉ መሆኑን ጠቁመው በዚህም አርብቶ አደሮቹ በግብርና ስራው በስፋት መሰማራት መጀመራቸውን ገልጸዋል።

በጉምቢ ቦርዶዴ ወረዳ የጎሎልቻ ቀበሌ ነዋሪ አርብቶ አደር መሀመድ ሙሳ በሰጡት አስተያየት በአካባቢያቸው የተገነባው የጎሎልቻ መስኖ ግድብ ለእንስሳቶቻቸው ውሃ በቅርበት እንዲያገኙ አስችሏቸዋል፡፡

''ከዚህ ቀደም ለእንስሳት ውሃ ፍለጋ ረጅም ርቀት እንሄድ ነበር'' ያሉት አርብቶ አደሩ መንግስት በውሃ አቅርቦት በኩል የነበረባቸውን ችግር በማቃለሉ እንደተደሰቱ ገልጸዋል፡፡

ግንባታው ከእንስሳት እርባታ በተጨማሪ በእርሻ ስራ በስፋት እንዲሳተፉ እድል እንደተፈጠረላቸው የተናገሩት ደግሞ ሌላኛው አርብቶ አደር ከድር ሰይድ ናቸው፡፡

በግብርና ስራው ተሰማርተው ኑሯቸውን ለማሻሻልም ወደ ስራ መግባታቸውን ነው የተናገሩት፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.