የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተቀናጀ የግብርና ስራን በመተግበር የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚያስችል ስራ እየተከናወነ ነው

Oct 27, 2025

IDOPRESS

🔇Unmute

አሶሳ፤ ጥቅምት 15/2018(ኢዜአ)፦ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተቀናጀ የግብርና ስራን በመተግበር የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚያስችል ስራ እየተከናወነ መሆኑን በብልጽግና ፓርቲ የክልሉ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢሳቅ አብዱልቃድር ተናገሩ።

በክልሉ ገጠር ቴክኖሎጂ ብዜትና የግብርና ሜካናይዜሽን ማስፋፊያ ኤጀንሲ በኡንዱሉ ወረዳ በ65 ሄክታር ማሳ ላይ እያለማ የሚገኘውን የተቀናጀ የግብርና ልማት ስራ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጎብኝተዋል።


በብልጽግና ፓርቲ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢሳቅ አብዱልቃድር በወቅቱ እንደገለፁት፤የግብርና ልማት ስራው በክልሉ ተቋማት የተቀናጀ የግብርና ስራን በመተግበር ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እያደረጉት ያለውን ተሳትፎ የሚያሳይ ነው።

የክልሉ ገጠር ቴክኖሎጂ ብዜትና የግብርና ሜካናይዜሽን ማስፋፊያ ኤጀንሲ እያከናወነ የሚገኘው የግብርና ስራ ለሌሎች ተቋማት አርአያ የሚሆን ተግባር ነው ብለዋል።

ኤጀንሲው በቆሎ፣ ማሽላ፣ ቄንቄስና የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬዎችን በማልማት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና ገበያን ለማረጋጋት የሚያስችል ስራ እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

ተቋማት ከመደበኛ ስራቸው ጎን ለጎን በተለያዩ የልማት ስራዎች እያደረጉት ያለው ተሳትፎ የውስጥ ገቢ አቅማቸውን ለማሳደግ የሚያግዝ መሆኑን ጠቅሰው፤ የአመራሩ ቁርጠኝነት እና ተነሳሽነት ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።


የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ገጠር ቴክኖሎጂ ብዜትና የግብርና ሜካናይዜሽን ማስፋፊያ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙስጠፋ ሙሐመድ፤ በበኩላቸው ኤጀንሲው የግብርና ስራን ለማዘመን እና በቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆን በራሱ አቅም እያከናወነ ያለው ስራ ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል።


ኤጀንሲው የዳቡስ ወንዝን በመጠቀም እያለማ ከሚገኘው የሰብል ልማት ጎን ለጎን የእንስሳት እርባታ በመጀመር የተቀናጀ የግብርና ስራ እያከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።

የተለያዩ የሰብል አይነቶችን በማልማትና ለገበያ በማቅረብ ህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ተጠቃሚ እየሆነ መምጣቱን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።

በመስክ ጉብኝቱ ላይ የክልሉ ምክርቤት አፈጉባኤ አስካለች አልቦሮን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እና የተለያዩ ወረዳ አመራሮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.