የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

የዳሰነቾች ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴ ''ጀለባ''

Oct 31, 2025

IDOPRESS

🔇Unmute

የዳሰነች ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴ ''ጀለባ''

(በጣፋጩ ሰለሞን ከጂንካ ኢዜአ ቅርንጫፍ)

ዳሰነቾች በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በደቡብ ኦሞ ዞን ውስጥ ከሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር በአብሮነት ተጎዳኝተው ይኖራሉ። የብሔረሰቡ አባላት ዋነኛ መተዳደሪያ ከብት እርባታ ሲሆን፤ ከከብት እርባታው ጐን ለጐን በዝቅተኛ ደረጃ በግብርናና በዓሳ ማስገር ስራ ይተዳደራሉ፡፡ ዳሰነቾች በሰሜን ከሐመር፣ በደቡብ ከኬኒያ፣ በምስራቅ ከቦረና በስተ ምዕራብ ደግሞ ከኛንጋቶም ማህበረሰብ ተጎራብተው ይኖራሉ።

ዳሰነቾች ከኩሽቲክ የቋንቋ ነገድ የሚመዘዝ ''አፍ ዳሰነች'' የተሰኘ የመግባቢያ ቋንቋም አላቸው። ዳሰነቾች የተለየ የአለባበስ፣ የአጋጌጥ፣ የቤት አሰራር እና የባህላዊ የሙዚቃ ስልተ ምትን ጨምሮ አስደማሚ ባህሎች እና ማራኪ የመልክዓ ምድር አቀማመጥን የታደሉ ናቸው።

ዳሰነቾች ከሚታወቁባቸው አስደማሚ ባህሎች ውስጥ አንዱ የሆነው አለመግባባቶችን በውይይት የሚፈቱበት የ''ጀለባ''ስርዓት ተጠቃሽ ነው። ይህ ስርዓት ግጭቱ ቂምና ቁርሾ በማይሻገርበት መልኩ በዘላቂነት የማስወገድ አቅም ያለው ሲሆን የማይናወጥ ሰላምና ወንድማዊ ትስስር እንዲጠናከርም ሚናው የጎላ ነው። ዕሴቱ የዳሰነቾች የአኗኗር ቁመና የሚለካበትና የሚመዘንበት መጻኢንም የሚተለምበትም ጭምር ነው። ስለሆነም በዳሰነቾች ዘንድ ቂም መያዝ አሎሎ ተሸክሞ እንደመዞር ይቆጠራል ነው የሚባለው።

የባህሉ ተመራማሪ ሊዮን አርሎት 'ጀለባ'' የተሰኘው ባህላዊ ዳኝነት ከአካባቢው ሰላም አልፎ ለቀጠናው ወንድማማችነት መጠናከር ትልቅ ሚና ያለው የፍትህ ስርዓት መሆኑን ያነሳሉ። በ''በጀለባ'' ስርዓት ባህላዊ የዳኝነት አሰጣጥ እርከኖች እንዳሉ ጠቅሰው፥ አለመግባባቶች ሲፈጠሩ ''ኖሞ'' የተሰኙ ሽማግሌዎች ወደ ስፍራው በማቅናት የግጭቱን መንስኤ በማጣራት ''ቶሎል'' ለተሰኙ ሌሎች ሽማግሌዎች የሚያሳውቁበት አሰራርም አላቸው።

እንደ ግጭቱ ቅለትና ክብደት ''ቶሎል'' በተሰኙ ሽማግሌዎች ተለይቶ ቀለል ያለው ''ካባና'' በተሰኙ ዳኞች ውሳኔ የሚሰጥ ሲሆን፥ ጉዳዩ ከበድ ያለ ከሆነ ደግሞ የመጨረሻው ውሳኔ ''አራ'' በተሰኙ ዳኞች ይሰጣል። ከነፍስ ማጥፋት በስተቀር ሁሉም ውሳኔዎች ''አራ'' በተሰኙ ዳኞች እልባት ያገኛሉ።

የነፍስ ማጥፋት ወንጀል ሲከሰት ግን ጉዳዩን ለመንግሥት አሳልፎ በመስጠት ጉዳዩ በፍርድ ቤት ውሳኔ እንዲያገኝ ይደረጋል ። ነፍስ ያጠፋው ሰው የእርምት ጊዜውን አጠናቆ ማህበረሰቡን ለመቀላቀል ሲወስን ባህላዊ የዕርቅ ስነ-ስርዓት ተዘጋጅቶ በዳይና ተበዳይ ይቅር የሚባባሉበትም ስርዓት እንዳለ የባህሉ ተመራማሪ ይናገራሉ።


በዳሰነቾች ባህል ልዩነቶች ሰላማዊ በሆነ መንገድ በዘላቂነት መንገድ የመፍታት ዘመናትን የተሻገረ ድንቅ ዕሴት መኖሩን የሚያነሱት የብሔረሰቡ አባል አሸቴ ነካሲያ፤ “በዳሰነች ብሔረሰብ ቂም መያዝ አሎሎ ተሸክሞ እንደመዞር ይቆጠራል'' ይላሉ። በዳሰነቾች አለመግባባቶች በውይይት የሚፈቱበት ስርዓት እንዳለ ጠቅሰው፥ ''ናብ'' በተሰኘው የዳኝነት ስፍራ አለመግባባቶች ውለው ሳያድሩ እልባት ያገኛሉ ብለዋል።

ሌላው የብሔረሰቡ አባል ሎቶያቡስ ሎኪሰሬሬ በበኩላቸው የባህል መሪዎች የተጣላን ማስታረቅ፣ ትውልዱን የመግራትና በስነ-ምግባር የማነፅ ኃላፊነት እንዳላቸው ጠቅሰዋል። ''ማንም ሰው ከባህል መሪዎች ትዕዛዝ አያፈነግጥም'' የሚሉት አቶ ሎቶያቡስ፥ ሁሉም እርስ በእርስ በመከባበር እና ችግሮች ሲኖሩ በውይይት በመፍታት አብሮነቱን ያጠናክራል ብለዋል።


ወጣቱ ለባህል መሪዎች ታዛዥ ነው የሚሉት ደግሞ ሌላው አስተያየት ሰጪ የብሔረሰቡ አባል ሎሲያ ሎብቻ ወጣቶች ለአካባቢው ሰላም ዘብ እንዲቆሙ፣ ከአጎራባች ህዝቦች ጋር በፍቅር እንዲኖሩ በማስተማር ወጣቱን በስነ-ምግባር የማነፅ ስራ እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

የዳሰነች ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደለ ሀቴ በበኩላቸው የዳሰነች ህዝብ ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴ ከወረዳው አልፎ ለቀጠናው ሰላም ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለዋል። የብሔረሰቡ ባህላዊ የሽምግልና ስርዓት ትውልዱን በመግራት በስነ- ምግባር የታነፀ ዜጋ እንዲፈጠር እንዳደረገም አስረድተዋል።


የጂንካ ዩኒቨርሲቲ የሶሻል አንትሮፖሎጂ መምህርና ተመራማሪ አጎናፍር ሰለሞን፤ ባህላዊ የዳኝነት ስርዓቶች ለዘመናዊው የፍትህ ስርዓት መጠናከር ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል ብለዋል። ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓቶች ቅጣት በመጣል ጥፋተኝነት እንዲሰማ የሚያደርጉ ሳይሆኑ፤ እውነተኛ ይቅርታን የሚያሰፍኑና ለአብሮነት የሚበጁ ዕንቁ ባህሎች እንደሆኑም አብራርተዋል።


ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎቹ በግለሰብ ተጠቃሚነት ላይ ሳይሆን በማህበረሰብ ተጠቃሚነት ላይ ትኩረት የሚያደርጉ በመሆናቸው ከዘመናዊው የፍትህ ስርዓት በይበልጥ ለአብሮነት መጠናከር አስተዋጽኦ እንዳላቸውም ገልጸዋል። ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎቹም ለሀገራዊ መግባባት ሚናቸው የላቀ በመሆኑ፥ እሴቶቹ ተጠብቀው፣ ለምተውና ጎልብተው ጥቅም ላይ እንዲውሉ መስራት እንደሚገባም መክረዋል።

ሀገራችን ቂምና ቁርሾን የወለዱ ያለመግባባቶች በዘላቂነት በሰለጠነና ሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በማቋቋም ሁሉንም ያሳተፈ ስራ እየሰራች እንደሆነ ያነሱት መምህርና ተመራማሪው አጎናፍር ሰለሞን ዕሴቶቹ በማህበረሰቡ ዘንድ ካላቸው ተቀባይነት እንዲሁም ሀገራዊ የምክክር ሂደቱን ከማገዝ አንጻር ጉልህ ሚና ስለሚኖራቸው መጠቀም እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.