የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በኦሮሚያ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት 6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ይቀርባል   

Nov 3, 2025

IDOPRESS

🔇Unmute

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 23/2018(ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት 6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ቡና ለማዕከላዊ ገበያ እንደሚቀርብ የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ሀላፊና የቡናና ሻይ ዘርፍ ሀላፊ አቶ መሃመድሳኒ አሚን ለኢዜአ እንደተናገሩት በክልሉ ባለፉት ዓመታት የቡና ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ የተከናወኑ ተግባራት ውጤት እያመጡ ናቸው።

በተለይም በክልሉ በቡና የተሸፈነ መሬትን ለማሳደግ እና ምርታማነቱን ለመጨመር ከግብርና ማዕከል የወጡ የተሻሻሉ ዝርያ ያላቸው የቡና ችግኞች በስፋት መተከላቸውን ገልጸዋል።


ከዚህ ጎን ለጎን ያረጁና ምርት መስጠት ያቆሙ የቡና ዛፎችን መጎንደልና ነቅሎ በአዲስ የመተካት ስራ በመሰራቱ የቡና ምርታማነት በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱንም ገልጸዋል።

ለቡና አምራች አርሶ አደሮችም የሚደረገው ድጋፍ በተሻለ መልኩ እየተከናወነ በመሆኑ የአምራቹ ተጠቃሚነትም እያደገ መጥቷል ነው ያሉት።

በ2017 ምርት ዘመን ከተሰበሰበው 15 ሚሊዮን ኩንታል የቡና ምርት ጥራቱን የተጠበቀ 5 ሚሊዮን ኩንታል ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን በማስታወስ።

በተያዘው በጀት አመት ደግሞ መጠኑን በማሳደግ 6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ቡና ለማዕከላዊ ገበያ እንደሚቀርብ ገልጸዋል።


ምርቱ ከብክነት በጸዳ መልኩ በጥራት እንዲሰበሰብም በልማቱ ላይ ለተሳተፉ ለሁለት ሚሊዮን አርሶ አደሮች እና ለ8 ሺህ በየደረጀው ላሉ የግብርና ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ግንዛቤ መሰጠቱን ተናግረዋል።

ቡና ጥራቱን በጠበቀ መልኩ ከመሰበሰብ ጀምሮ ገበያ እስኪደርስ ድረስ ያልተቋረጠ ክትትልና ድጋፍ እንደሚያስፈልገው አስረድተዋል።

በሌላ በኩል በክልሉ ከሻይ ልማት የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ ኢንሼቲቭ ተቀርጾ ወደስራ መገባቱን አስታውሰው በኢሉአባቦር፤ በቡኖ በደሌና በጅማ ዞኖች የሻይ ልማት በስፋት እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።


የሻይ ልማቱ በ1ሺህ 490 ሄክታር መሬት ላይ በኩታ ገጠም እየተከናወነ ሲሆን ይህም አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ከማድረግ በላይ ለአካባቢው ማህበረሰብ ሰፊ የስራ እድል መፍጠር መቻሉን ገልጸዋል።

በተለይ ልማቱን በማጠናከር ከዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ከባለሀብቶች ጋር በተፈጠረ ትስስር በሶስቱ ዞኖች የሻይ ቅጠል ፋብሪካዎች ለማቋቋም እንቅስቃሴ መጀመሩን አክለዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.