🔇Unmute
ጂንካ፤ ህዳር 3/2018(ኢዜአ)፦ ጂንካ ዩኒቨርሲቲ የእንስሳት ዝርያን በማሻሻልና የወተት ምርታማነትን በማሳደግ ለሌማት ትሩፋት ውጤታማነት የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ገለጸ።
መንግስት በግብርናው ዘርፍ በነደፋቸው ስትራቴጂዎች የአርሶ አደሩና የአርብቶ አደሩ ህይወት እየተቀየረ ነው ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት እንደ ሃገር ተግባራዊ የተደረገው የሌማት ትሩፋት መርሀ ግብርም በእንስሳት ሃብት ልማት ላይ የራሱን ተጨማሪ አቅም በመፍጠር ተጠቃሚነታቸውን እያሳደገው ነው።

በዚህም አርሶና አርብቶ አደሩ እንስሳትን በዘመናዊ መንገድ በማርባት የተመጣጠነ ምግብ ከማግኘት ባለፈ ከቤት ፍጆታ የተረፈን ምርት ለገበያ በማቅረብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ማሳደግ ችለዋል።
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ተስፋዬ አለሙ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በአካባቢው ካለው ከፍተኛ የእንስሳት ሀብት ማህበረሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን ዘርፉን በጥናትና ምርምር የመደገፍ ሥራ እየተሰራ ነው።

የእንስሳት ሀብቱ ከፍተኛ ቢሆንም እርባታው ባለመዘመኑ የሚፈለገው ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እየተገኘ አይደለም ብለዋል።
ችግሩን ለመፍታት ዩኒቨርሲቲው በጥናትና ምርምር የእንስሳት ዝርያን በማሻሻል ምርታማነታቸውን ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም ላሞችን በማዳቀልና የመኖ አቅርቦት ላይ በተሰራው ሥራ የወተት ምርታማነትን በእጥፍ ማሳደግ ተችሏል ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው የእንስሳት ዝርያን በማሻሻልና የመኖ አቅርቦትን በማስፋት ለሌማት ትሩፋት ውጤታማነት የድርሻውን እየተወጣ መሆኑንም ገልጸዋል።
በዩኒቨርሲቲው የእንስሳት ጤና ሳይንስ የትምህርት ክፍል ኃላፊና የእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ተመራማሪ እያሱ ልፋሞ ፤በተቋሙ በሰው ሰራሽ ዘዴ ላሞችን በማዳቀል ሴት ጥጃዎችን ብቻ እንዲወልዱ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ተግባራዊ መደረጉን ገልጸዋል።

ይህም የወተት ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ጠቅሰው፣ በባህላዊ ዘዴ ከሚረቡ ላሞች በቀን ይገኝ የነበረን አነስተኛ የወተት ምርት ወደ 15 ሊትር ከፍ ለማድረግ መቻሉን በማሳያነት ተናግረዋል።
የእንስሳቱን ዝርያ በማሻሻልና ጤናቸውን በመጠበቅ ምርታማነትን ለማሳደግ ዩኒቨርሲቲው የጀመራቸው የምርምር ሥራዎች በቀጣይም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመልክተዋል።
ዩኒቨርሲቲው ከዝርያ ማሻሻል ሥራው ጎን ለጎን የተሻሻሉ የእንስሳት መኖ ዝርያዎችን በማስፋፋት ምርታማነትን ለማሳደግ እየሰራ መሆኑንም አቶ እያሱ አመልክተዋል።
የዩኒቨርሲቲው ሀብት ልማትና ገቢ ማመንጨት ሥራ አስፈፃሚ ከማል አህመድ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ከአምስት ዓመት በፊት በሙከራ ደረጃ በ12 የተሻሻሉ ላሞች የጥናትና ምርምር ሥራ መጀመሩን ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት በቀን በአማካይ ከ10 እስከ 15 ሊትር ወተት የሚሰጡ ከ40 በላይ ላሞች እንዳሉ ጠቁመው፣ የወተት ምርቱን ወደ 24 ሊትር ከፍ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የደቡብ አሪ ወረዳ አርሶ አደር ሀዝሚ ገበየሁ በበኩላቸው፤ በአካባቢው ያሉ የወተት ላሞች ምርታማነት አነስተኛ በመሆኑ ከቤት ፍጆታ የዘለለ ጥቅም ሳያገኙ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።
ጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት ጋር በመቀናጀት የተሻሻሉ የወተት ላም ዝርያዎችን የማዳቀል ሥራ እንደሚሰራ ገልጸው፣ ይህም የወተት ምርታማነታቸውን እያሳደገው መምጣቱን ተናግረዋል።

የባካዳውላ አሪ ወረዳ ነዋሪ አቶ ዘለቀ አድማሱ በበኩላቸው የአካባቢው ላሞች በቀን እስከ 2 ሊትር ወተት ብቻ እንደሚሰጡ አስታውሰው፣ ከተዳቀሉ የወተት ላሞች 10 ሊትርና ከዚያ በላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው በ2017 በጀት ዓመት በአሪ ዞን እና በደቡብ ኦሞ ዞን 1ሺህ 100 ላሞችን በሰው ሰራሽ የማዳቀል ዘዴ ከተሻሻሉ የወተት ላም ዝርያዎች ጋር የማዳቀል ሥራ አከናውኗል።
የእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ሥራው ለአርብቶ አደሩን በቁጥር ላይ ብቻ የተመሰረተን የእርባታ ዘዴን በማዘመን የተሻለ ገቢ የሚያገኝበት ሁኔታ እየፈጠረ መሆኑም ተመላክቷል።
አዲስ አበባ፤ የካቲት 21/2017(ኢዜአ)፡- የምግብ ዋስትና እና ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ለነገ የሚተው የምርጫ ጉዳይ ባለመሆኑ በልዩ ትኩረት መረባረብ እንደሚገባ...
Feb 28, 2025
ሐረር፤ የካቲት 16/2017(ኢዜአ)፦ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ ሁሉን አቀፍ ስራዎች የህዝቡን ተጠቃሚነት ያሳደጉ መሆናቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ ጥር 30/2017(ኢዜአ)፦የየካቲት ወር የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ በጥር ወር በነበረበት የሚቀጥል መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስ...
Feb 8, 2025