
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 28/2017(ኢዜአ)፦ የገቢዎች ሚኒስቴር የታክስና ቀረጥ ስርዓትን ዲጂታላይዝ ለማድረግ እያከናወነ ያለውን ተግባር አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስገነዘበ።
ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 28ኛ መደበኛ ስብሰባው የገቢዎች ሚኒስቴር የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን ገምግሟል።
በምክር ቤቱ የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በገቢዎች ሚኒስቴር ፖሊሲዎችና መመሪያዎች ተግባራዊ መደረጋቸው ገቢ እንዲጨምር ማድረጉን አመልክቷል።
የታክስና ቀረጥ ስርዓትን ዲጂታላይዝ ለማድረግ የተጀመረው ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ነው የጠቆመው።
የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በገቢ አሰባሰብ፣ በታክስ ህግ ተገዥነት፣ በኮንትሮባንድ ቁጥጥርና ሌሎች የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን አቅርበዋል።
ተቋሙ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 646 ነጥብ 72 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 653 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን ገልጸዋል።
አፈጻጸሙ ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ279 ቢሊዮን ብር ወይንም ከ74 በመቶ በላይ ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል።
ከተሰበሰበው ገቢ የሀገር ውስጥ ታክስ 345 ነጥብ 93 ቢሊዮን ብር፣ የውጭ ንግድ ቀረጥና ታክስ 307 ነጥብ 27 ቢሊዮን ብር ድርሻ እንደሚይዙ ጠቁመዋል።

እንደሚኒስትሯ ገለጻ፤ ከተሰበሰበው ገቢ ውስጥ በተሻሻለው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ቀመር መሰረት 61 ነጥብ 13 ቢሊዮን ብር ለክልሎች የተላለፈ ሲሆን፤ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ16 ቢሊዮን ብር በላይ እድገት አሳይቷል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት 15 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የሚገመት የገቢና ወጪ ኮንትሮባንድ እቃዎችና ህገ-ወጥ ገንዘብ መያዙንም ተናግረዋል።
ገቢን መደበቅ፣ ግብይትን ያለደረሰኝ ማከናወን፣ ኮንትሮባንድ፣ የግብር ስወራና የታክስ ማጭበርበር አሁንም የታክስ አስተዳደር ችግሮች መሆናቸውን አንስተዋል።
ህገ ወጥነትን ለመከላከል በግብይት ወቅት ደረሰኝ በማይቆርጡ 616 ድርጅቶች ላይ ኦፕሬሽን በማከናወን 597 ተጠርጣሪዎች ለህግ በማቅረብ በወንጀል ምርመራና ክስ ሂደት ላይ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።
የምክር ቤት አባላት በቀረበው ሪፖርት ላይ በታክስና ጉምሩክ ህግ ተገዥነት፣ የታክስ ምንጭ ከማስፋት፣ ኮንትሮባንድን ከመከላከልና ህገ-ወጥ ኬላን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ አስተያየትና ጥያቄዎችን አንስተዋል።
የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ የታክስ አሰባሰብ ስርዓቱን ለማዘመንና የታክስ ምንጮችን ለማስፋት ልዩ ትኩረት ከተሰጣቸው ተግባራት መካከል መሆናቸውን ገልጸዋል።
የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ በበኩላቸው፤ ህገ-ወጥ ኬላዎችን በጥናት መለየታቸውን ገልጸው፤ ችግሩን ለመከላከል ከጸጥታ አካላት፣ ከፍትህ ተቋማትና ከክልሎች ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በምክር ቤቱ የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ደሳለኝ ወዳጆ በሚኒስቴሩ ፖሊሲዎችና መመሪያዎች ተግባራዊ መደረጋቸው ገቢ እንዲጨምር አድርጓል ብለዋል።
የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ከሚያመነጨው አኳያ የሚሰበሰበውን ገቢ የበለጠ ለማሳደግ የታክስና ቀረጥ ስርዓትን ዲጂታላይዝ ለማድረግ የተጀመረው ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
በተመሳሳይ የታክስ መሰረትን ማስፋት፣ ከክልሎች ጋር ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር፣ ከቀረጥ ነጻ የሚገቡ እቃዎች ለታለመላቸው አላማ መዋላቸውን ማረጋገጥ ትኩረት እንዲሰጣው አሳስበዋል።
ጅማ፤ ሚያዝያ 16/2018 (ኢዜአ)፡- በጅማ ዞን ባለፉት ዘጠኝ ወራት 52 ሺህ ቶን ቡና ለገበያ መቅረቡን የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ቲጃኒ ተማም ተናገሩ...
Apr 24, 2026
ጅግጅጋ፤ ሚያዝያ 13/2018 (ኢዜአ)፦ የኅብረት ሥራ ማኅበራትን በቴክኖሎጂና ሌሎች መስኮች የማጠናከር ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሠ መ...
Apr 22, 2026
አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 6/2018(ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በስንዴ ልማት ያስመዘገበችው ስኬት ለአፍሪካዊያን በምሳሌነት የሚጠቀስ መሆኑን የአ...
Apr 15, 2026
አዶላ ፤መጋቢት 30/2018 (ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን በበልግ አዝመራ ከ260 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ገለጸ...
Apr 9, 2026