ጎንደር፤ ጥር 5/2017(ኢዜአ)፡- የጥምቀት በዓልን ለማክበር ወደ ጎንደር የሚመጡ ቱሪስቶች የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክን እንዲጎበኙ ዝግጅት ማድረጉን የፓርኩ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡
ባለፉት ስድስት ወራት ፓርኩን የጎበኙ የውጪ ሀገር ቱሪስቶች ቁጥር መሻሻል ማሳየቱም ተጠቁሟል፡፡
የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ማሩ ቢያድግልኝ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ የፓርኩን የቱሪስት ፍሰት ለመጨመር በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ መገናኛ ዘዴዎች ፓርኩን የማስተዋወቅ ስራ እየተከናወነ ነው፡፡
በጥምቀት በዓል በርካታ ቱሪስቶች ወደ ጎንደርና አካባቢው የሚመጡበት አመቺ ወቅት መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚሁ አጋጣሚ ጎብኚዎች ፓርኩን እንዲጎበኙ ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል፡፡
የፓርኩ መዳረሻ የሆኑ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ጥገናን ጨምሮ የጎብኚዎችን ምቾት መጠበቅ የሚያስችሉ የቱሪስት ማረፊያ ስፍራዎችን መሰረተ ልማት የማሟላት ስራ መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡
በአካባቢው የሰፈነው ሰላም ለቱሪስቶች ቁጥር መጨመር አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቅሰው፤ ባለፉት ስድስት ወራትም አንድ ሺህ የሚጠጉ የውጪ ሀገር ቱሪስቶች ፓርኩን መጎብኘታቸውን አስረድተዋል፡፡
ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ወቅት ከ400 የማይበልጡ ጎብኚዎች ፓርጉን መጎብኘታቸውን አስታውሰው፤ ሆኖም ዘንድሮ የቱሪስቶች ቁጥር መሻሻል የታየበትና ተስፋ ሰጪ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡
ቱሪስቶቹ ከእስራኤል፣ ከፖላንድ፣ ከአሜሪካ፣ ከታይላድና ከቻይና የመጡ ሲሆን የአካባቢው ማህበረሰብም ለቱሪስቶች በሰጠው አገልግሎት ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን ተናግረዋል፡፡
ፓርኩ ከመግቢያ ትኬትና ከፊልም አገልግሎት ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ገልጸዋል፡፡
የቱሪስቶችን የቆይታ ጊዜ የሚያራዝሙና ፍሰቱንም ለመጨመር የሚያግዙ የቱሪዝም ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል፡፡
ፓርኩ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ዋልያ፤ ቀይ ቀበሮና ጭላዳ ዝንጀሮን ጨምሮ የብርቅዬ የዱር እንስሳትና አዕዋፋት መገኛ ስፍራ መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡
አዲስ አበባ ፤የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት ተገልጋዮች ፋይዳ መታወቂያን ተጠቅመው በዲጂታል አማራጭ ትኬት የሚቆርጡበት አሰራር ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ ጥር 03/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን የለማ የትራንስፖርት ኦፕሬተሮችንና የጭነት ባለቤቶችን የሚገናኝ መተግበሪያ አስጀምሯል። ...
Feb 12, 2025