የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
ህይወት እና ጉዞ

<p>በሐረሪ ክልል በምግብና ስርዓተ ምግብ ላይ የተመዘገቡ አበረታች ውጤቶችን ማስፋት ይገባል</p>

Jan 18, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ ጥር 9/2017(ኢዜአ)፦ በሐረሪ ክልል ባለፉት ዓመታት በተሰራው ስራ በምግብና ስርዓተ ምግብ ላይ የተመዘገቡ አበረታች ውጤቶችን ማስፋት እንደሚገባ የክልሉ ፕሬዝዳንት ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጃሚ መሀመድ ገለጹ።

የሐረሪ ክልል የምግብ ስርዓትና ኒውትሪሽን ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት በክልሉ በወረዳ ደረጃ የምግብ ስርዓትና ኒውትሪሽን ምክር ቤት ማብሰሪያ እና ስራ ማስጀመሪያ መርሀ ግብር አካሂዷል።

የክልሉ ፕሬዝዳንት ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጃሚ መሀመድ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የህጻናት እና እናቶችን ሥርዓተ ምግብ ማሻሻል ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶታል።

በክልሉ ባለፉት ዓመታት በሰቆጣ ቃልኪዳን መርሀ ግብር የተስተካከለ የስርዓተ ምግብ እንዲኖር ለማስቻል በተሰራው ስራ አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውንም ገልፀዋል።


ይህንን ተከትሎም በጨቅላ ህፃናት ላይ ይስተዋል የነበረው የመቀንጨር እና የመቀጨጭ ችግሮች እየቀነሱ መምጣታቸውን ጠቁመዋል።

በቀጣይም በሰቆጣ ቃል ኪዳን ትግበራ የተገኙ ተሞክሮዎችን በማስፋት የመጠነ መቀንጨር ችግርን ሙሉ ለሙሉ ለመፍታት በትኩረት መስራት እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት።

የስርዓተ ምግብ ችግር አሁንም ከፍተኛ ትኩረት የሚሻ አጀንዳ በመሆኑ በክልል ደረጃ የምግብ ስርዓትና የኒውትሪሽን ምክር ቤት ተቋቁሞ ደንብ በማፅደቅ ወደ እንቅስቃሴ መገባቱንም ጠቁመዋል።

የስርዓተ ምግብ ችግርን በዘላቂነት ለመቅረፍ ሰፊ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የኒውትሪሽን አማካሪ አቶ አብዱናሲር አህመድ በበኩላቸው የህፃናት መቀንጨርን ለመከላከል ማህበረሰቡ ዘንድ የስርዓተ ምግብ ለውጥ መፍጠር እንደሚገባ ገልጸዋል።


በተለይ የህፃናትን መቀንጨር ለመከላከል ህፃናት በቀን ውስጥ ማግኘት የሚገባቸውን የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ ለማስቻል ግንዛቤ ሲፈጠር መቆየቱንም አመልክተዋል።

በዚህም በክልሉ የአመጋገብ ስርዓት ለውጥ መደረጉን ተከትሎ በአጥቢ፤ ነፍሰጡር እና ዕድሜያቸው ከ2 አመት በታች ባሉ ህፃናት ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ አበረታች ውጤቶች ማስመዝገብ መቻሉን ገልጸዋል።

በተለይም በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተተገበረ የሚገኘው የሌማት ትሩፋት እና የከተማ ግብርና የማህበረሰቡን የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባሻገር በሂደት የተስተካከለ የምግብ ስርዓት እንዲኖር በማስቻል የህፃናት የመቀንጨር ምጣኔ እንዲቀንስ ማስቻሉንም ነው የገለጹት።

በቀጣይም የምግብ ስርዓትና የኒውትሪሽን ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቱ የምግብ ስርዓትና የኒውትሪሽን ተግባራት እንዲጠናከሩ አስፈላጊውን የድጋፍና ክትትል ስራዎች እንደሚያደርግ መናገራቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.