የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
ህይወት እና ጉዞ

<p>ኢትዮጵያ ከካርቦን ግብይት ስትራቴጂካዊ ጥቅሟን እንድታረጋግጥ እየተሰራ ነው</p>

Feb 6, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ጥር 28/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት የምታደርገውን ጥረት ለማሳካትና ከካርቦን ግብይት ስትራቴጂካዊ ተጠቃሚ እንድትሆን እየተሰራ መሆኑን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ስዩም መኮንን ገለጹ።


የዓለም አቀፍና የሀገር ውስጥ የካርቦን ገበያ ተሳትፎዎች በሥርዓት እንዲመሩ የሚያስችል ብሔራዊ የካርበን ግብይት ስትራቴጂ በመዘጋጀት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።


የኢትዮጵያ ብሔራዊ ካርቦን ግብይት ስትራቴጂ ዝግጅት ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ የሀገር ውስጥ፣የልማት አጋር ሀገራትና ድርጅቶች የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት በአዲስ አበባ ተካሂዷል።


ኢትዮጵያ በፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት አካታችነትን፣ ተጠያቂነትንና ዘላቂ ልማት ማስፋፋት ላይ መሰረት ያደረገ የካርቦን ግብይት ዕድሎችን ለመጠቀም ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላት ይታወቃል።


ለዚህም በኪዮቶ ፕሮቶኮል፣ በታዳሽና ንፁህ የልማት ስልት (ሲዲኤም)፣ የፈቃደኝነት የካርቦን ደረጃዎች ላይ በባለብዙ ወገን እና በሁለትዮሽ ደረጃ የተለያዩ ተሳትፎዎችን እያደረገች ትገኛለች።


የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ስዩም መኮንን እንደገለጹት፥ ሀገሪቱ ለሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀት ቅነሳና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት የ10 ዓመት መሪ የልማት እቅድ ቀርጻ ስትራቴጂካዊ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ናት።


የአረንጓዴ አሻራ፣በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የአየር ንብረት ለውጥ እቅድ፣የታዳሽ ኃይል ልማትና የኤሌክትሪክ ፕሮግራም፣ የሞተር አልባ ተሽከርካሪ ኢኒሼቲቭና ሌሎች ስራዎችን በማሳያነት ጠቅሰዋል።


ከዚህ አኳያ የካርቦን ግብይትን በውጤታማነት ለመምራትና ተጠቃሚ ለመሆን ብሔራዊ የካርበን ግብይት ስትራቴጂ በማዘጋጀት ላይ መሆኗን ገልጸዋል።


ይህም ኢትዮጵያ በፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት አንቀጽ-6 እና ሌሎች ህጋዊ አሰራሮች መሰረት በዓለም አቀፍ የካርበን ግብይት ላይ ውጤታማ ተሳትፎ በማድረግ ተጠቃሚ ለመሆን እየሰራች ነው ብለዋል።


የኢትዮጵያ ብሔራዊ ካርቦን ግብይት ስትራቴጂም ይህንን በማሳካት ረገድ ጉልህ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው።


ስትራቴጂው ግልጽ፣ የዳበረና ሀገራዊ ግቦችን በሚያሳካ መልኩ እንዲዘጋጅ ባለድርሻ አካላት በሂደቱ እንዲሳተፉ እየተደረገ ነው ብለዋል።


በመድረኩ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር፣የዓለም አቀፍ አጋር የልማት ተቋማት እና በኢትዮጵያ የሀገራት ኤምባሲ የስራ ኃላፊዎች እና ተወካዮች ተገኝተዋል።


በዚሁ ወቅትም የካርቦን ግብይት ሥርዓትን የሚያመላክት ሀገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ልምድና ተሞክሮ የሚያሳዩ የመነሻ ጽሁፎች ቀርበው ምክክር ተካሂዶባቸዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.