ሀዋሳ፤ጥር 28/2017 (ኢዜአ):- በኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ የተነደፉ ፕሮግራሞች ያስገኙትን ተጨባጭ ውጤት በሁሉም አካባቢዎች ማስፋት እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስታወቀ።
የምክር ቤት አባላትን ጨምሮ የግብርና ሚኒስቴር፣ የፌዴራልና የክልል ባለድርሻ አካላት በሲዳማ ክልል ሁለት ወረዳዎች እየተከናወነ ያለውን የመስኖ ልማት ስራ ተመልክተዋል።
በህዝብ በተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ላሌ በወቅቱ እንደገለጹት፥ የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ የተነደፉ አዳዲስ ኢንሼቲቮች ዘርፈ ብዙ ውጤት እያስመዘገቡ ነው።
በተለይም በግብርናው ዘርፍ የተነደፉ ፕሮግራሞች ተጨባጭ ለውጥ እያመጡ መሆናቸውን አንስተው ለውጡን በሁሉም አካባቢዎች በማስፋት በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ጉልህ ሚና መጫወት ይገባል ብለዋል።
በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በሰብል ልማት በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች የሚከናወኑ የልማት ስራዎች የአርሶአደሩን ህይወት የሚቀይሩና ከድህነት ለመውጣት የሚደረገውን ትግል የሚያግዙ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በሲዳማ ክልል በሆርቲካልቸር ዘርፍ አትክልትና ፍራፍሬን በመስኖ በማልማት የተገኘው ውጤት ለሌሎች ተሞክሮ የሚሆን መሆኑን ጠቅሰዋል።
በተለይም ዝናብ አጠር በሆነው ሀዋሳ ዙሪያ ወረዳ በመስኖ የሚለማው መሬት የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና በማረጋገጥ አካባቢውን ከአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ የታደገ ነው ብለዋል።
የሲዳማ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ሃላፊ አቶ መምሩ ሞኬ በክልሉ በዘንድሮ የበጋ መስኖ ከ72 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በሁለት ዙር በሚከናወነው የመስኖ ልማት ስራ የቤተሰብ ብልጽግና ለማረጋገጥ የተቀመጡ ፓኬጆችን መሰረት ያደረገና በዋናነት በአምስት የአትክልት ልማት ዘርፎች ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ለዚህም በ25 ወረዳዎች 581 በላይ ክላስተሮችን በማደራጀት ከ22 ሺህ በላይ ሄክታሩ የመስኖ ልማት ስራ በኩታገጠም የሚለማ መሆኑን ገልጸዋል።
ለመስኖ ልማት ስራ በቂ ግብዓት መቅረቡን የጠቀሱት አቶ መምሩ "ዘመናዊ የመስኖ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ ሌሎች የውሃ አማራጮችን በመጠቀም እየተከናወነ ያለው ስራ ውጤታማ ነው" ብለዋል።
የመስኖ ልማት ስራው ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በመሬት ሽፋንና ምርት፣ እንዲሁም ለድጋፍና ክትትል ምቹ በሆነው የኩታገጠም ስራ የተሻለ መሆኑን ገልጸዋል።
በሀዋሳ ዙሪያ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ሃጊርሶ ደበላ በበኩላቸው በ12 ሄክታር መሬት ላይ ቲማቲም ጨምሮ የተለያዩ አትክልቶችን በመስኖ እያለሙ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በመስኖ ልማት ስራው ለበርካታ ወገኖች የስራ እድል ከመፍጠር ባሻገር ገበያን ማረጋጋት የሚያስችል ምርት እያመረቱ መሆኑን ገልጸዋል።
በመስክ ምልከታው ላይ የግብርና ሚኒስቴር የስራ ሀላፊዎች፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትና ከተለያዩ ክልሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
አዲስ አበባ ፤የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት ተገልጋዮች ፋይዳ መታወቂያን ተጠቅመው በዲጂታል አማራጭ ትኬት የሚቆርጡበት አሰራር ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ ጥር 03/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን የለማ የትራንስፖርት ኦፕሬተሮችንና የጭነት ባለቤቶችን የሚገናኝ መተግበሪያ አስጀምሯል። ...
Feb 12, 2025