የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
ህይወት እና ጉዞ

<p>ብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያ ህገ ወጥነትን በመከላከል ፍትሐዊ የንግድ ውድድር እየፈጠረ ነው - የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ</p>

Feb 8, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ የካቲት 1/2017(ኢዜአ)፡- ብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያ ህገ ወጥ ንግድን በመከላከል በንግዱ ማህበረሰብ ዘንድ ፍትሐዊ ውድድር እንዲፈጠር ማስቻሉን የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ገለጸ፡፡

በኢትዮጵያ የነዋሪዎችን የመታወቅ መብት ለማረጋገጥ፣ በአገልግሎት ሰጭና ተቀባዮች መካከል መተማመን እንዲዳብር፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ግልጽነት ተጠያቂነትና የተሳለጠ አሰራር ስርዓት ለማንበር የዲጂታል መታወቂያ ገቢራዊ ተደርጓል።

በዚህም የኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያ በአዋጅ ቁጥር 1284/2015 ተቋቁሞ ወደ ስራ የገባ ሲሆን እስካሁን 12 ሚሊዮን ያህል ነዋሪዎች የዲጂታል መታወቂያ ባለቤት ለመሆን ተመዝግበዋል።

ኢትዮጵያ በ2030 በአፍሪካ የዲጂታል ትስስር፣ አካታች የፋይናንስ ስርዓትና ቀልጣፋ አገልግሎትን ለማረጋገጥ በምታደርገው ጥረት ብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያ ሚናው የጎላ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የደንበኞች አገልግሎት ዳይሬክተር አስቴር ዘውዴ ፤ ፋይዳ እንደ ስሙ ለአገልግሎት ሰጭም ሆነ ተቀባይ ፋይዳው ብዙ መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡

ብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያ ህገ ወጥ እንቅስቃሴን በመከላከል በህግ ላይ የተመሰረተ የንግድ ሥርዓት ለመፍጠር የጎላ አበርክቶ እንዳለውም ገልጸዋል፡፡

የተጭበረበረ ደረሰኝን ለመከላከል፣ ህገ ወጥ ንግድን ለመቆጣጠር ብሎም ፍትሃዊ የንግድ ውድድር መፍጠር ያስችላል ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያውን ከግብር ከፋዮች መለያ ቁጥር ጋር በማስተሳሰር አብዛኛው ነጋዴ ወደ ሥርዓቱ እንዲመጣ ተደርጓል ነው ያሉት፡፡

የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ፋይዳን ቀድሞ ገቢራዊ ማድረግ መጀመሩን የገለጹት ዳይሬክተሯ፤ ለመንግስትም ሆነ ለግብር ከፋዮች ገንቢ አገልግሎት እየሰጠ ነው ብለዋል፡፡

ቢሮው የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር ለመስጠት የባዮሜትሪክስ አሻራ ይወስዱ እንደነበር አስታውሰው፤ ከፋይዳ በኋላ አሻራ መወሰድ ማቆማቸውን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም የባዮሜትሪክስ አሻራ ድግግሞሹን በመቀነስ የመንግስትንና የነጋዴዎችን ጊዜና ወጪ መቆጠብ ማስቻሉንም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.