ሚዛን አማን፤ የካቲት 3/2017 (ኢዜአ)፡-በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ሚዛን አማን ከተማ ሀገር አቀፍ የንግድ ትርኢትና ባዛር ተከፈተ።
ባዛሩ የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ሲሆን ከባዛሩ የሚገኘው ገቢ ለከተማዋ የኮሪደር ልማት ሥራ እንደሚውል ተመላክቷል።
የከተማዋ ከንቲባ አቶ ግሩም ተማም ባዛሩን ሲከፍቱ እንደገለጹት፣ ባዛሩ አምራቾች ምርታቸውን በቀጥታ ለማህበረሰቡ እንዲያቀርቡ ዕድል የሚሰጥ ነው።
ይህም ሸማቹ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ በመግዛት ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ የኢኮኖሚ መነቃቃትን ይፈጥራል ብለዋል።
የኮሪደር ልማቱን ለማፋጠን የሚያስችል ገቢ ለማግኘት ታቅዶ መዘጋጀቱንም ነው የገለጹት።
በከተማው ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ የሚፈጅ የኮሪደር ልማት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የጠቀሱት ከንቲባው፣ የከተማዋ ነዋሪዎች ለልማቱ በገንዘብ ከሚያደርጉት ድጋፍ በተጨማሪ በባዛሩ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ አስገንዝበዋል።
የባዛሩ መዘጋጀት የንግድ ትስስርን ለመፍጠር ዕድል ይሰጣል ያሉት ደግሞ የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ አምሳለ ነጋሽ ናቸው።
ባዛሩ ምርቶች ለማስተዋወቅ ፋይዳ እንዳለው ጠቅሰው፣ ከባዛሩ የሚገኘውን ገቢ ለአካባቢው ልማት ለማዋል መታቀዱን ጠቅሰዋል።
በባዛሩ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የመጡ ከ100 በላይ ነጋዴዎች መሳተፋቸውን ጠቅሰዋል።
ከአዲስ አበባ ከተማ ዘመናዊ የቤት ውስጥ መገልገያ ቁሶችን ይዘው በባዛሩ ላይ የተገኙት አቶ አዲስ ደረጀ እንዳሉት፣ በእቃዎቻቸው ላይ ቅናሽ አድርገው መቅረባቸውን ተናግረል።
"ባዛሩ ምርቶቻቸውን በቀጥታ ለሸማቹ ማህበረሰብ ከማድረስ ባሻገር ከአካባቢው ነጋዴዎች ጋር በመተዋወቅ የንግድ ትስስር ለመፍጠር ያስችላል" ብለዋል።
ከጅማ ከተማ በመምጣት የሪች ሳሙና ምርቶች ያቀረቡት ወይዘሮ ሰዓዳ ሰይድ በበኩላቸው፣ ባዛሩ ምርቶቻቸውን ለኅብረተሰቡ ለማስተዋወቅ እንደሚያግዛቸው ገልጸዋል።
እስከ የካቲት 16 ቀን 2017 ዓ.ም በሚቆየው ባዛር ላይ የተለያዩ አልባሳት፣ የቆዳ ውጤቶች፣ መዋቢያዎች፣ የቤት ውስጥ ቁሶች፣ የኤሌክትሮኒክስና ሌሎች የቴክኖሎጂ ውጤቶች በስፋት ቀርበዋል።
አዲስ አበባ ፤የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት ተገልጋዮች ፋይዳ መታወቂያን ተጠቅመው በዲጂታል አማራጭ ትኬት የሚቆርጡበት አሰራር ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ ጥር 03/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን የለማ የትራንስፖርት ኦፕሬተሮችንና የጭነት ባለቤቶችን የሚገናኝ መተግበሪያ አስጀምሯል። ...
Feb 12, 2025