ሆሳዕና፤ የካቲት 5/2017(ኢዜአ)፡- በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ችግር ፈቺ የፈጠራ ስራዎችን በማፍለቅና በማስፋፋት የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ አስታወቀ።
ችግር ፈቺ የፈጠራ ውጤቶችን ከክልላዊ ልማትና ከዘላቂ የስራ እድል ፈጠራ ጋር አስተሳስሮ ለማስተግበር የተዘጋጀ የምክክር መድረክ ዛሬ በሆሳዕና ተካሂዷል።
የቢሮው ኃላፊ አቶ ሰላሙ አማዶ በወቅቱ እንደገለጹት የምክክር መድረኩ በክልሉ ችግር ፈቺ የፈጠራ ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ የማድረግ ዓላማን የያዘ ነው።
በክልሉ ችግር ፈቺ የፈጠራ ስራዎችን በማልማት የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከከፍተኛ እንዲሁም ከቴክኒክና ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ተቋማቱ የበርካታ የፈጠራ ስራዎች መፍለቂያ በመሆናቸው ከስራ እድል ፈጠራና ልማታዊ ስራዎች ጋር በማስተሳሰር ለለውጥ መስራት ይገባል ብለዋል።
ባለፈው አንድ ዓመት በክልሉ ከተሰሩ 100 የፈጠራ ስራዎች 25ቱ በአምዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ባለስልጣን እውቅና እንደተሰጣቸውም ገልጸዋል።
የክልሉ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ኃላፊ አቶ አሰፋ ደቼ በበኩላቸው በክልሉ የሚገኙ የቴክኒክ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ቴክኖሎጂን የመቅዳት፣ የመተግበርና የማሸጋገር ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም የግብርናና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን ጨምሮ ከ600 በላይ የማህበረሰቡን ችግር መሰረት ያደረጉ የፈጠራ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
በዘርፉ ተጨባጭ ውጤት ለማምጣት ከሁሉም ባለድርሻዎች ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል።
የማህበረሰቡን ችግር የሚፈቱ የፈጠራ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የኢንዱስትሪና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር አቶ ሙሉነህ መንገሻ ናቸው።
የእንሰት መፋቂያ ማሽንን ጨምሮ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋለውን ችግር መቅረፍ የሚያስችሉ ሶፍትዌሮችን ማበልፀግ መቻሉን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
በተቋሙ የተጀመሩ የፈጠራ ስራዎች በተለያዩ ተቋማት እውቅና ማግኘታቸውን ተከትሎ ወደ ማህበረሰቡ በስፋት ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
አዲስ አበባ ፤የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት ተገልጋዮች ፋይዳ መታወቂያን ተጠቅመው በዲጂታል አማራጭ ትኬት የሚቆርጡበት አሰራር ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ ጥር 03/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን የለማ የትራንስፖርት ኦፕሬተሮችንና የጭነት ባለቤቶችን የሚገናኝ መተግበሪያ አስጀምሯል። ...
Feb 12, 2025