አዲስ አበባ፤ የካቲት 5/2017(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋሙ የግብርና ስርዓቶችን በመተግበር የምግብ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ እየሰራች መሆኑን የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ገለጹ።
ዓለም አቀፍ የመስኖ ልማትና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ምርታማነት ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
በጉባኤው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ የአየር ንብረት ለውጥና የምግብ ዋስትና ችግር እየተባባሰ መሆኑን ገልጸዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አመራር ሰጭነት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ማህበረሰብ አቀፍ የግብርና ልማት ሽግግርን እውን የሚያደርጉ ተግባራትን በአርዓያነት እየፈጸመች ነው ብለዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋምን ታሳቢ ያደረጉ የምግብ ምርታማነት ሥራዎችን እያከናወነች መሆኗን ጠቅሰው፥ ለአብነትም የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርን ጠቅሰዋል።
በዚህ መርሐ ግብር ከ40 ቢሊዮን በላይ ችግኝ መትከላችን የደን ሽፋንን ከማሳደጉ በላይ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የምግብ ዋስትናቸውን እያረጋገጡ መሆኑን ተናግረዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የግብርና ኢኒሼቲቭ የስንዴ ልማት መሆኑን ጠቅሰው፥ በዚህም ከውጭ የሚገባን ስንዴ በማቆም የስንዴ ምርት ፍጆታዋን በራሷ አቅም ማምረት ችላለች ብለዋል።
ይህም አፍሪካ ራሷን መመገብ እንደምትችል ማረጋገጫ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፥ ለመስኖ፣ ለሜካናይዜሽንና ሌሎች የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋሙ የግብርና ስርዓቶች ትኩረት በመስጠት የምግብ ሉዓላዊነቷን ታረጋግጣለች ብለዋል።
ኢትዮጵያ የሌማት ትሩፋትን በመጀመር በቤተሰብ ደረጃ የተመጣጠነ የምግብ ስርዓትን የሚያረጋግጡ የወተት፣ የእንቁላል፣ የማርና ሌሎችንም ምርቶች ላይ በማተኮር ውጤታማ ስራዎችን እየሰራች መሆኑንም ጠቅሰዋል።
አፍሪካም ሌማቷን መሙላት የሚያስችላት አቅም አላት ያሉት ፕሬዚዳንቱ የኢትዮጵያ ተሞክሮ ለአህጉሪቱ የሚተርፍ እንደሆነም አንስተዋል።
በመስኖ ልማት መርሀ ግብሩ አርብቶ አደሮችም እየተሳተፉ መሆኑን ጠቁመው የመስኖ ፕሮጀክቶቻችን የምግብ ዋስትናንና የማይበገር የግብርና ስርዓት መገንባትን ዓላማ ያደረጉ ናቸው ብለዋል።
አፍሪካውያን የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ለመስኖ ልማት፣ ለግብርና ኢንቨስትመንት፣ ለቴክኖሎጂና ለመረጃ ጥራት ትኩረት እንዲሰጡም ጠይቀዋል።
የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ዘመኑን የዋጁ ፖሊሲና ስትራቴጂዎችን በመተግበር የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማሳደግ እንዲሁም የፋይናንስ ዘርፍን በማጠናከር የአፍሪካ ግብርናን ለመለወጥ መስራት ይገባል ብለዋል፡፡
ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የግብርና ስርዓትን ለመገንባት ከሀገራት ተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር የተጣጣሙ ስልቶችን መከተልም ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት የግብርና፣ የገጠር ልማት፣ የብሉ ኢኮኖሚ፣ የዘላቂ አካባቢ ኮሚሽነር ጆሴፋ ሳኮ፥ ግብርና ለአህጉሪቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የጀርባ አጥንት ነው ብለዋል፡፡
በመጨው ጊዜያት የአህጉሪቱን ህዝብ መመገብ የሚያስችል ምርትን ለማሳካት የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም እና ዘላቂነት ያለው ግብርና እና ስርዓተ ምግብ ሊተገበር እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
አፍሪካውያን በጋራ ከሰሩ ርሃብን ማስወገድ፣ የአየር ንብረት ለውጥን በብቃት መቋቋምና የትውልዱን የብልፅግና መሻት ማሳካት እንደሚችሉም ተጠቁሟል።
በመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር የተዘጋጀው ይህ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ዛሬን ጨምሮ ለሶስት ቀናት የሚካሄድ ይሆናል።
አዲስ አበባ ፤የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት ተገልጋዮች ፋይዳ መታወቂያን ተጠቅመው በዲጂታል አማራጭ ትኬት የሚቆርጡበት አሰራር ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ ጥር 03/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን የለማ የትራንስፖርት ኦፕሬተሮችንና የጭነት ባለቤቶችን የሚገናኝ መተግበሪያ አስጀምሯል። ...
Feb 12, 2025