ሚዛን አማን፤ የካቲት 6/2017(ኢዜአ)፡- ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የቤንች ሸኮ ዞን የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
የቤንች ሸኮ ዞን አስተዳደር በበኩሉ ለሕዳሴው ግድብ ግንባታ የመጨረሻ ምዕራፍ ሥራ የሚውል 8 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለማሰባሰብ እየሠራ መሆኑን አስታውቋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ ሰሎሞን ማቴዎስ፣ የሕዳሴው ግድብ ሁሉንም በአንድ ያስተሳሰረ የአብሮነት ፕሮጀክታችን ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም ለሁለት ጊዜ ቦንድ መግዛታቸውን አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅትም ከደመወዛቸው ቦንድ ለመግዛት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
የሕዳሴው ግድብ የኢትዮጵያውያን የእንችላለን ወኔ ነጸብራቅ ነው ያሉት ደግሞ አቶ ተሰማ ሻሪ የተባሉ የከተማዋ ነዋሪ ናቸው።
በጫና ውስጥ ግድቡን መገንባት የተቻለው ኢትዮጵያውያን አብሮነታቸውን በማጠናከራቸው እንደሆነ ገልጸው፣ በሌሎች የልማት ሥራዎችም ሕብረትን ማጠናከር ይግባል ብለዋል።
ወይዘሮ ፋንታነሽ ካሳ የተባሉ ሌላኛዋ ነዋሪ በበኩላቸው፣ የሕዳሴው ግድብ የግንባታ ሥራ ከተጀመረ አንስቶ ቦንድ በመግዛት የድርሻቸውን ሲወጡ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
በቀጣይም የግድቡ ግንባታ ተጠናቆ ለአገልግሎት እስኪበቃ ድረስ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
የሕዳሴው ግድብ የእኛ ዘመን ትውልድ አሻራ ያረፈበትና ዘመን የሚሻገር ፕሮጀክት በመሆኑ በቦንድ ግዥና በተለያዩ መንገዶች የምናደርገው ድጋፍ መቀጠል አለበት ብለዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሁሉም አሻራ ያረፈበት የጋራ ሀብታችን ነው ያሉት ደግሞ የዞኑ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ እሸቱ ሻንበል ናቸው።
የግድቡ ግንባታ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ በመድረሱ ትልቅ ኩራት እንደሚሰማቸው ገልጸው፣ ቀሪ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ በዞኑ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ከማህበረሰቡ 8 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ገቢ ለማሰባሰብ ታቅዶ በሁሉም መዋቅሮች ገቢ የማሰባሰብ ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም በተለያዩ ጊዜያት ከዞኑ 38 ሚሊዮን ብር ድጋፍ መደረጉን አስታውሰው፣ በቀሪ ጊዜያትም ድጋፉን አጠናክረው ለማስቀጠል ይሰራል ብለዋል።
ህብረተሰቡ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ከማስተባበር ባሻገር በራሳቸው የ5 ሺህ ብር ቦንድ ግዥ ለመፈጸም ቃል መግባታቸውን የገለጹት ኃላፊው፣ ዕቅዱን ለማሳካት የተጠናከረ ሥራ ይሰራል ነው ያሉት።
አዲስ አበባ ፤የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት ተገልጋዮች ፋይዳ መታወቂያን ተጠቅመው በዲጂታል አማራጭ ትኬት የሚቆርጡበት አሰራር ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ ጥር 03/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን የለማ የትራንስፖርት ኦፕሬተሮችንና የጭነት ባለቤቶችን የሚገናኝ መተግበሪያ አስጀምሯል። ...
Feb 12, 2025