የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
ህይወት እና ጉዞ

<p>የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ዘላቂና ቀጣይነት ያለው የምጣኔ ሃብት ዕድገት ለማስመዝገብ መሰረት ያኖረ ነው</p>

Feb 14, 2025

IDOPRESS

አሶሳ፤የካቲት 6/2017(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ተግባራዊ የተደረገው አካታች የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ዘላቂና ቀጣይነት ያለው የምጣኔ ሃብት ዕድገት ለማስመዝገብ ጥሩ መሰረት ያኖረ መሆኑን በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሐብት መምህር ሙሐመድ ኢብራሂም ገለጹ።


በኢትዮጵያ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ከሐምሌ 2016 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ መደረጉ ይታወቃል።


አጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሸያው ተግባራዊ በመደረጉም በአገሪቷ የወጪና ገቢ ንግድ ማነቆዎችን በመፍታት፤ የንግድ ሚዛንን በማስተካከል፤ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን በማሳደግ የአገሪቷን የቆየ የኢኮኖሚ ስብራት ለመጠገን የሚያስችል መሆኑ ይነሳል።


በዚሁ ጉዳይ ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሐብት መምህር ሙሐመድ ኢብራሂም፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሸያው የአገሪቷን ምጣኔ ሃብት ከውድቀት በመታደግ ዘላቂና አስተማማኝ እድገት እንዲኖር የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።


የግብርናው ዘርፍ ብቻውን የሀገሪቷን ኢኮኖሚ እንዲሸከም ተደርጎ መቆየቱ ለብዙ ችግሮች መዳረጉን አንስተው፥ ለውጡን ተከትሎ የተለያዩ ዘርፎች ዋና ዋና የእድገት ምሰሶዎች ተደርገው መወሰዳቸው ትልቅ እመርታ መሆኑን ተናግረዋል።


በመሆኑም በኢትዮጵያ ተግባራዊ የተደረገው አካታች የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ዘላቂና ቀጣይነት ያለው የምጣኔ ሃብት ዕድገት ለማስመዝገብ ጥሩ መሰረት ያኖረ ነው ብለዋል።


መንግስት የወሰደው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ከግብርናው ዘርፍ በተጨማሪ የአገልግሎት፣ የኢንዱስትሪ፣ የቱሪዝምና ሌሎች ዘርፎችን ያካተተ በመሆኑ የብዝሃ የኢኮኖሚ ዕድገት መሰረት ያስቀመጠ መሆኑንም አብራርተዋል።


የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የሀገር ውስጥ ምርትን በማበረታታት፣ የወጭና ገቢ ንግድ ሚዛንን ለመጠበቅ፣የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለማቃለልና ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ፍቱን መፍትሄ መሆኑንም አንስተዋል።


የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም የብድር አቅርቦት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ጤናማ መሆኑን አመላካች እንደሆነ ማሳያ መሆኑን አንስተዋል።


በቀጣይም የፋይናንስ ተቋማትን ማጠናከር፣የሥራ ዕድል ፈጠራን ማሳደግ እና የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ላይ በትኩረት መስራት ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.