ቀደምት ፓን አፍሪካዊነት አቀንቃኞች አንዱ ህልማቸው በኢኮኖሚና ፖለቲካ የተሳሰረች፣ ራስ በቅ አፍሪካን ዕውን ማድረግ ነበር። ጥሬ ዕቃዎቿ ላይ እሴት የሚጨምሩ ኢንዱስትሪዎች ባለቤት የሆነች፣ ከውጭ ምርቶች ጥገኝነት የተላቀቀችና በምግብ ራሰ በቅ የሆነች፣ በበይነ-ቀጣናዊ የኢኮኖሚና ንግድ የተሳሰረች አፍሪካን ዕውን ማድረግ ነበር ጽኑ መሻታቸው።
ለዚህም አንዳንድ የአፍሪካ መንግስታት ከቅኝ ግዛት ነጻ በወጡ ማግስት ጀምሮ በፖለቲካዊና በኢኮኖሚ ራስን ለመቻል ስትራቴጂ ነድፈዋል። ለዚህ ደግሞ ግዙፍ አፍሪካ በቀል ኩባንያዎችን መስርቶ ምርታማነትን መጨመር፣ ሀገራትን በልማት ማስተሳሰር እና ብርቱ አህጉር አቀፍ የግል ዘርፍ መገንባት የሞከሩ አሉ። ባለሙያዎችም ከመንግስት መር ኢኮኖሚ ልማት ይልቅ ለዘላቂ ዕድገት የግል ዘርፍ መራሽ አፍሪካ አቀፍ ኢኮኖሚ መገንባት እንደሚያሻ ይወተውታሉ።
የአፍሪካ የኢኮኖሚ ውህደትና ትስስር በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ወቅት ቢቀነቀንም አህጉራዊ የስምምነት ማዕቀፍ ሆኖ የወጣው በአፍሪካ ሕብረት አስቸኳይ ውሳኔ በፈረንጆቹ 2018 ነበር። ይሄውም አፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነት ነው። ከ2021 ጀምሮ ተግባራዊ መሆን ጀምሯል። ስምምነቱን 54 አባል ሀገራት ፈርመዋል። 48ቱ ሀገራት በሕግ መወሰኛ ምክር ቤቶቻቸው አፅድቀውታል።
የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነት ማዕቀፍ ታዲያ የግል ዘርፋን የሚያበረታታ ነው። ይህ ደግሞ በአፍሪ ሀገራት የሚገኙ ከበርቴዎች ከትውልድ ሀገራቸው ተሻግረው በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱና አፍሪካ አቀፍ ኢኮኖሚያዊ ትስስርና ተጠቃሚነት እንዲጎለብት መልካም ዕድል ይዞ ይመጣል።
ናይጄሪያዊው ከበርቴ አሊኮ ዳንጎቴ የአፍሪካ የግሉ ዘርፍ ቁንጮ ናቸው። በፎርብስ መጽሔት መረጃ በተያዘው ዓመት የ67 ዓመቱ ቢሊየነር ዳንጎቴ 23 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ሀብት አካብተዋል። ዳንጎቴ በአፍሪካ ኢንቨስመንትቻውን እያሰፉ ነው። ይህ እንቅስቃሴያቸው ደግሞ የራስ በቅና የበይነ-አፍሪካዊያን ትስስር ተምሳሌቱ ቱጃር ያሰኛቸዋል።
አሊኮ ዳንጎቴ ከሰሞኑ ወደ አዲስ አበባ ጎራ ብለው ለኢትዮጵያ አዳዲስ መረጃዎችን አብስረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ን ጨምሮ ከተለያዩ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ጋር መክረዋል። ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲግ ዋና ስራ አስፈፃሚ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) ጋር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በኢትዮጵያ ያላቸውን የሲሚንቶ ምርት መጠን በዕጥፍ ለማሳደግ ወስነዋል።
ከማዕድን(ሲሚንቶ) በተጨማሪም በሌሎችች ኢንቨስትመንት አማራጮች ለመሰማራት የአዋጭነት ገበያውን እየፈተሹ ስለመሆኑ እንዲሁ። ለአብነትም የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ መገንባትን ጨምሮ የግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን በሚያሳድጉ ዘርፎች ለመሰማራት አቅደዋል። በስኳር ልማት እንዲሁ።
ናይጄሪያዊው የአፍሪካው ቀዳሚው ባለሃብት አሊኮ ዳንጎቴ በሲሚንቶ፣ የነዳጅ ማፈላለግ፤ የማዕድን ማውጣት፤ የማዳበሪያ እና የተፈጥሮ ጋዝ ማጓጓዝ ስራዎች ላይ በስፋት ተሰማርተዋል። ናይጄሪያን ጨምሮ በ20 የአፍሪካ ሀገራት በቢሊዮኖች ዶላር የሚገመት ኢንቨስትመንት አፍስሰዋል። ለአብነትም በሲሚንቶ ዘርፍ ከናይጄሪያ በተጨማሪ በኢትዮጵያ፣ ታንዛንያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ዛምቢያ፣ ሴኔጋል፣ ካሜሮን፣ ኮንጎ ሪፐብሊክ፣ ጋና እና ኮትዲቭዋር የሲሚንቶ ፋብሪካ ገንብተዋል።
በናይጄሪያ ሌጎስ የአፍሪካ ግዙፉን የዳጅ ማጣሪያ ገንብተዋል። ስገንብተዋል። የነዳጅ ማጣሪያው ጋና እና ደቡብ አፍሪካን ጨምሮ በአፍሪካ ሀገራት ነዳጅ ይልካል። ኩባንያው የአውሮፕላን ነዳጅን ወደ አውሮፓ ለመላክም አቅዷል። ከባድ ናፍጣ የመላክ እቅድ አለው። የዳንጎቴ ነዳጅ ማጣረያ የአፍሪካ የነዳጅ ጥገኝነት ለመቀነስ ተስፋ ተሰንቆበታል።
ኩባንያቸው በግብርና፣ ምግብ ማቀነባበሪያ፣ በስኳር፣ በፋይናንስ አገልግሎት፣ መሰረተ ልማትና ኢነርጂ፣ ማዳበሪያ፣ በምግብ እና መጠጥ እና ቴሌኮሙኒኬሽን፣ ኮንስትራክሽን እና ሌሎች ዘርፎች በኢንቨስትመንት ተሰማርቷል። አሁንም አፍሪካን እያካለለ ነው። ቱጃሩ ዳንጎቴ በብረታ ብረት፣ በታዳሽ ኃይል፣ በጤና እና ፋርማሲዩቲካል ዘርፎችም ያላቸውን ኢንቨስትመንት በአፍሪካ ሀገራት ውስጥ የማስፋት ግብ ይዘዋል።
የአሊኮ ዳንጎቴ እንቅስቃሴ ከቀደምት ፓን አፍሪካዊያን ህልም ጋር የተጣጣመ ነው። አፍሪካን በአፍሪካ በቀል ኢንዱስትሪ ማልማት፣ ስራ ዕድል መፍጠር፣ ከውጭ ምርት ጥገኝነትን መቀነስ፣እሴት የተጨመረባቸወን የአፍሪካ ምርቶች ወደ ሌሎች አህጉራት መላክና አፈሪካዊያን ማስተሳሰር ለዚህ ሁነኛ አብነት ናቸው። ዳንጎቴን መሰል የግሉ ዘርፍ ተዋንያን ለአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነት ትግበራ ውጤታማነት ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ።
ለአህጉራዊ አጀንዳዎች ስኬት የግሉ ዘርፍ ምሰሶ በመሆኑ ለአፍሪካ ዘላቂ ዕድገት የመንግስታት እና የግሉ ዘርፍ እጅና ጓንት መሆንን ይጠይቃል። የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች የሁልጊዜም ምክረ ሀሳብ ነው።
አዲስ አበባ ፤የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት ተገልጋዮች ፋይዳ መታወቂያን ተጠቅመው በዲጂታል አማራጭ ትኬት የሚቆርጡበት አሰራር ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ ጥር 03/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን የለማ የትራንስፖርት ኦፕሬተሮችንና የጭነት ባለቤቶችን የሚገናኝ መተግበሪያ አስጀምሯል። ...
Feb 12, 2025