የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
ህይወት እና ጉዞ

<p>ከተማ አስተዳደሩ በ622 ሚሊዮን ብር ወጪ አዲስና ነባር የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ እያካሄደ ነው</p>

Feb 25, 2025

IDOPRESS

ጎንደር፤ የካቲት 17/2017(ኢዜአ)፡- በጎንደር ከተማ በ622 ሚሊዮን ብር ወጪ የሕብረተሰቡን የልማት ጥያቄ መመለስ የሚያስችሉ አዲስና ነባር የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ።

በከተማ አስተዳደሩ በመሰረተ ልማት፣ በከተማ ግብርና፣ በሥራ ዕድል ፈጠራና በኑሮ ውድነት ቅነሳ የተከናወኑ ተግባራትን የሚገመግም መድረክ እየተካሄደ ነው።


በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የከተማና መሰረተ ልማት መምሪያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙሉጌታ ታደሰ በመድረኩ እንደገለጹት፣ በበጀት ዓመቱ 26 አዲስና 13 ነባር የልማት ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ ይገኛሉ።

በበጀት ዓመቱ በ622 ሚሊዮን ብር ወጪ እየተከናወኑ ያሉ ፕሮጀክቶች የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄዎች መመለስ የሚያስችሉ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።

ከፕሮጀክቶቹ መካከል የውስጥ ለውስጥ የጠጠር መንገዶች ከፈታ፣ የመለስተኛ ድልድዮች ግንባታ፣ የጎርፍ መፋሰሻ ቱቦዎች ቁፋሮና ጥገና ሥራ ይገኙበታል ብለዋል።


ከነባር ፕሮጀክቶች ውስጥ የአምስት ኪሎ ሜትር የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ መንገድ ሥራ፣ የ2 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ ሥራና የጎርፍ ማፋሰሻ ግንባታ ሥራዎች እንደሚጠቀሱ ገልጸዋል።

ከአዳዲስ የልማት ፕሮጀክቶች መካከል አምስት የወጣት መዝናኛ ማዕከላት ግንባታ ሥራ የሚገኙበት ሲሆን የማዕከላቱ ዲዛይን ሥራም ተጠናቆ በጨረታ ሂደት ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል።


የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው በበኩላቸው በከተማው የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና የመልካም አስተዳደር ቅሬታዎችን ለመፍታት በርብርብ በመሰራቱ አመርቂ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት በጥንካሬና በድክመት የታዩ አፈጻጸሞችን በመገምገም በጥንካሬ የሚነሱትን በግብአትነት ለመጠቀም መድረኩ ጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል።


በጎንደር ከተማ የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ዘመናዊ የግብርና ምርቶች ግብይት ማዕከል ግንባታ ሥራ እየተፋጠነ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ሃላፊ አቶ ቴዎድሮስ ጸጋዬ ናቸው።

የግብይት ማዕከሉ በ160 ሚሊዮን ብር ወጪ ግንባታው እየተፋጠነ መሆኑንም ተናግረዋል።

የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበራት በኩል በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ ለማቅረብ ከተማ አስተዳደሩ 25 ሚሊዮን ብር ብድር መልቀቁንም አቶ ቴዎድሮስ ጠቁመዋል።

በመድረኩ በቀረበው የአፈጻጸም ሪፖርት ላይ ውይይት የተካሄደ ሲሆን የሴክተር ተቋማት የሥራ ሃላፊዎች፣ የከተማ አስተዳደሩና የክፍለ ከተሞች አመራሮች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.