የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
ህይወት እና ጉዞ

<p>በክልሉ የአርሶ አደሩን የቁጠባ ባህል በማሳደግ ከ80 ሚሊዮን ብር በላይ ለማሰባሳብ ተችሏል</p>

Feb 27, 2025

IDOPRESS

ዲላ፤ የካቲት 19/2017 (ኢዜአ)፡-በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሕብረት ሥራ ማህበራትን ሪፎርም በማድረግ የአርሶ አደሩን የቁጠባ ባህል ለማሳደግ በተሰራው ሥራ ከ80 ሚሊዮን ብር በላይ ለመቆጠብ መቻሉን የክልሉ ሕብርት ሥራ ልማት ኤጄንስ አስታወቀ።

በክልሉ ቁጠባን ባህል ያደረገ ማህበረሰብ በመፍጠር ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር በርብርብ እየተሰራ መሆኑም ተመላክቷል።

የኤጀንሲው ምክትል ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ድንቅነሽ በራቆ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በክልሉ የህብረት ሥራ ማህበራት የአባሎቻቸውን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አንጻር ሰፊ ክፍተት አለባቸው።

በተለይ ከአደረጃጀትና ከፋይናንስ አቅም አንጻር የነበረባቸውን ውስንነት ለመፍታት በተከናወነ የሪፎርም ሥራ ከ765 በላይ ማህበራት መታጠፋቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ከ6ሺህ 200 የሚበልጡ ማህበራትን መልሶ በማደራጀትና በማጠናከር የፋይናንስ አቅማቸውን ለማሳደግ በተደረገ ጥረት ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ከአባሎቻቸው 80 ሚሊዮን ብር በቁጠባ ለማሰባሰብ መቻሉን አስረድተዋል።

በክልሉ ቁጠባን ባህል ያደረገ ማህበረሰብ በመፍጠር ከተረጂነት ወደምርታማነት ለመሸጋገር በየደረጃው በርብርብ እየተሰራ መሆኑንም ሥራ አስኪያጇ ገልጸዋል።

አርሶ አደሩ ከግብርና ምርት ሽያጭ የሚያገኘውን ገቢ በመቆጠብ ከተረጂነት በመውጣት በራስ አቅም ለመንቀሳቀስ የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዝም ጥሪ አቅርበዋል።

በዞኑ ኅብረት ሥራ ማህበራትን መልሶ በማደራጀት የኢኮኖሚ አቅማቸውን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ያነሱት ደግሞ የጌዴኦ ዞን ህብረት ሥራ ልማት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ብርሃኑ ተካዬ ናቸው።

በአደረጃጀት፣ በቁጠባ አቅም እና በመሰል መለኪያዎች ከደረጀ በታች የሆኑና በገጠር ቀበሌያት የሚገኙ 126 የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ሥራ ማህበራትን በሪፎርም በማዋሃድ 10 ጠንካራ ማህበራትን ለመፍጠር እንደተቻለም አስረድተዋል።

በማህበራቱ ውስጥ የሚገኙ 9 ሺህ አባላት ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲቆጥቡ በአሁኑ ወቅት የንቅናቄ ሥራ መጀመሩንም ገልጸዋል።

የንቅናቄ ስራው በተጀመረ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ ቁጠባ መሰብሰቡን ጠቅሰዋል።

"የዳበረ የቁጠባ ባህል ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ መሰረታዊ ነው" ያሉት ሃላፊው፣ አርሶ አደሩ የቁጠባ ባህሉን በማዳበር በቀጣይ የተሻለ ሕይወት ለመምራት እራሱን ማዘጋጀት እንዳለበት አሳስበዋል።

በዞኑ የኮቾሬ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጌታቸው ታሪኩ በበኩላቸው በገጠር ቀበሌያት ሕብረት ሥራ ማህበራትን በማደራጀት አርሶ አደሩ በቅርበት እንዲቆጥብ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ በወረዳው የቁጠባ ንቅናቄን በማስጀመር በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ ለማስቆጠብ በዘመቻ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በወረዳው የቡኖ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ብርሃኑ ቦጋለ በበኩላቸው እንዳሉት በዕቅድ አለመመራት፣ የቁጠባ ባህላቸው ደካማ መሆን እንዲሁም በአካባቢያቸው ጠንካራ የቁጠባ ማህበር አለመኖር የገንዘብ አቅማቸው ዝቅተኛ እንዲሆን አድርጓል።

የግብርና ምርት በተለይ ቡናን ለገበያ አቅርበው የሚያገኙትን ገቢ በመቆጠብ በቀጣይ የፋይናንስ አቅማቸውን ለማሳደግ ከወዲሁ ቁጠባ መጀመራቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.