አዲስ አበባ፤የካቲት 20/2017(ኢዜአ)፡-ልማት የብሪክስ አባል ሀገራት ትብብር ዋነኛ የትኩረት ማዕከል መሆን አለበት ሲሉ በብሪክስ ጉዳይ የኢትዮጵያ ዋና አስተባባሪ (ሼርፓ) እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምህረቱ ገለጹ።
በብራዚል ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የብሪክስ ጉዳይ ዋና አስተባባሪዎች እና ምክትል አስተባባሪዎች ስብሰባ ትናንት ማምሻውን ተጠናቋል።
በስብሰባው ማብቂያ በብራዚል ፕሬዝዳንት ሉዊስ ኢናሲዮ ሉላ ዳ ሲልቫ የተመራ የከፍተኛ አመራሮች ምክክር ተካሄዷል።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ እና የኢትዮጵያ የብሪክስ ጉዳይ ዋና አስተባባሪ አቶ ማሞ ምህረቱ የተመራው እና ምክትል አስተባባሪ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ የተካተቱበት ልዑካን ቡድን በስብስባው ላይ ተሳትፏል።
ዋና አስተባባሪው(ሼርፓ) አቶ ማሞ ምህረቱ ኢትዮጵያ የባለብዝሃ ወገን ትብብር፣የጋራ ደህንነት እና ዘላቂ ልማት በቁርጠኝነት እንደምትሰራ ገልጸዋል።
ከጤና ጋር በተገናኘ የብሪክስ ሀገራት የዓለም የጤና አደጋዎችን ለመመከት የሚያስችላቸውን የጤና መሰረተ ልማቶች የሟሟላት ጉዳይ ልብ ሊሉት እንደሚገባ አመልክተዋል።
ከኢኮኖሚ እና ንግድ በተያያዘም የብሪክስ የትብብር ማዕቀፍ ልማትን ዋነኛ የማስተሳሰሪያ መንገድ ማድረግ እንዳለበት ተናግረዋል።
የገበያ ተደራሽነት፣ የልማት ፋይናንስ የማሰባሰብ አቅምን ማሳደግ፣ መሰረተ ልማቶችን ማሟላት እና ኢንቨስትመንት የመሳብ አቅም ትኩረት የሚያሻቸው ጉዳዮች ናቸው ብለዋል ዋና አስተባባሪው።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ አማካኝነት የካርቦን ልቀትን መጠን መቀነስ መቻሏን የገለጹት አቶ ማሞ፥ ድንጋይ ከሰልን በታዳሽ ኃይል የመተካት ኢኒሼቲቭ እየተገበረች እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የብሪክስ አባል ሀገራት የፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ማዕቀፍ (ዩኤንኤፍሲሲ) ገቢራዊነት እና ውጤታማነት አበክረው እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል።
በተባበሩት መንግስታት የዲጂታል ቴኮኖሎጂ እና ሰው ሰራሽ አስተውሎት ዓለም አቀፍ ትብብር ማዕቀፍ አማካኝነት በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት የሰው ሰራሽ አስተውሎት አቅም እና አስተዳደርን ማጠናከር እንደሚገባ አንስተዋል።
ዋና አስተባባሪው ኢትዮጵያ ብሪክስ እንዲጠናከር እና ሁሉን አካታች እንዲሆን በቁርጠኝነት ትሰራለች ብለዋል።
የብራዚል ፕሬዝዳንት ሉዊስ ኢናሲዮ ሉላ ዳ ሲልቫ፥ ብራዚል በብሪክስ ፕሬዝዳንነቷ በዓለም አቀፍ የጤና ትብብር፣ ሁሉን አካታች የሰው ሰራሽ አስተውሎት አስተዳደር እና የዓለም የኢኮኖሚ እና የፋይናንስ መዋቅር ማሻሻያ በትኩረት እንደምትሰራ ገልጸዋል።
ውጤታማ የአየር ንብረት ለውጥ የፋይናንስ ስርዓት መፍጠር፣ የደቡብ-ደቡብ ትብብርን ማጠናከር እና ተቋማዊ አቅም ግንባታ ሌሎች የትኩረት አጀንዳዎች ናቸው ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ሉላ የብሪክስ ሀገራት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ማዕቀፍ መሰረት የባለብዝሃ ወገን ትብብርን የማጠናከር ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
ዋና አስተባባሪው(ሼርፓ) አቶ ማሞ ምህረቱ ከስብሰባው ጎን ለጎን ከብራዚል ኢንዶኔዢያ፣ ሩሲያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ህንድ እና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ሼርፓዎች ጋር ውይይት አድርገዋል።
ውይይቱ የሀገራቱን የጋራ ግቦች ለማሳካት በትብብር መስራት እና የሁለትዮሽ ትስስርን ማጠናከር በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ያተኮረ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
አዲስ አበባ ፤የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት ተገልጋዮች ፋይዳ መታወቂያን ተጠቅመው በዲጂታል አማራጭ ትኬት የሚቆርጡበት አሰራር ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ ጥር 03/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን የለማ የትራንስፖርት ኦፕሬተሮችንና የጭነት ባለቤቶችን የሚገናኝ መተግበሪያ አስጀምሯል። ...
Feb 12, 2025