የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
ህይወት እና ጉዞ

<p>በትምህርት ዘርፍ የሰው ሰራሽ አስተውሎት አጠቃቀምን በስርዓትና በጥንቃቄ መምራት ያስፈልጋል</p>

Feb 28, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ የካቲት 20/2017(ኢዜአ)፦ በትምህርት ዘርፍ የሰው ሰራሽ አስተውሎት አጠቃቀምን በስርዓትና በጥንቃቄ መምራት እንደሚያስፈልግ ትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ።

የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ''የሰው ሰራሽ አስተውሎት በትምህርት ዘርፍ የሚያመጣው ዕድልና የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን መፍታት'' በሚል መሪ ሃሳብ 3ኛውን ዓለም አቀፍ የጥናትና ምርምር ጉባዔ በአዲስ አበባ ማካሄድ ጀምሯል።


የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ኮራ ጡሹኔ እንዳሉት በአሁኑ ወቅት የሰው ሰራሽ አስተወሎት በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተስፋፋ ይገኛል ብለዋል።

ቴክኖሎጂው በትምህርቱ ዘርፍም በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ ቢሆንም አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ መምጣቱን ገልጸዋል።

ሰው ሰራሽ አስተውሎት ጊዜን ለመቆጠብ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተመሳሳይ ቴክኖሎጂን ለመጠቀም አጋዥ የመሆኑን ያህል አጠቃቀሙ ጥንቃቄ ካልተደረገበት አደጋው የከፋ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ጥናትና ምርምሮችን፣ የማለፊያና የምዘና ፈተናዎችን በስፋት በሰው ሰራሽ አስተውሎት የመስራት ልምምድ እየተስተዋለ መሆኑን ገልጸው ይህም ለትምህርት ዘርፉ ፈታኝ ነው ብለዋል።

በመሆኑም የሰው ሰራሽ አስተውሎት አጠቃቀምን በስርዓትና በጥንቃቄ መምራት የግድ መሆኑን በአፅንኦት ተናግረዋል።

ለዚህም የትምህርት ተቋማት የአሰራር ስርዓታቸውን ማሻሻል፣ የህግና የፖሊሲ ማዕቀፎቻቸውን መፈተሽና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የቁጥጥር ስራቸውን ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ(ዶ/ር) በበኩላቸው ቴክኖሎጂን በሁሉም ዘርፎች የማስፋት ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

ቴክኖሎጂን በአግባቡ መጠቀም ካልተቻለ የሚያስከትለው ጉዳት የከፋ በመሆኑ በእውቀትና በጥንቃቄ ላይ የተመሰረተ አጠቃቀምን ማጎልበት ያስፈልጋል ብለዋል።

ለዚህም በሰው ሰራሽ አስተውሎት ላይ የተዘጋጀው ጉባዔ የተሻለ ልምድን ለመቅሰም እና የአሰራር ማሻሻያዎችን በመለየት መፍትሔ ለማመላከት በእጅጉ ያግዛል ነው ያሉት።

የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ብርሃነመስቀል ጠና (ዶ/ር)፤ በትምህርት ዘርፍ የሰው ሰራሽ አስተውሎት አጠቃቀም ላይ ክፍተቶች መኖራቸውን ገልጸዋል።

የጥናትና ምርምር ሥራዎች በሰው ሰራሽ አስተውሎት እየተሰሩ መሆናቸውን አንስተው ይህም የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የተጀመረውን ጉዞ ወደ ኋላ ይጎትተዋል ነው ያሉት።

የጥናትና ምርምር ጉባኤው በሰው ሰራሽ አስተውሎት አጠቃቀም ላይ ያሉ ጉድለቶችን ለማረምና የሚያስከትሉትን ጉዳት አስቀድሞ ለመከላከል የሚያግዙ ሀሳቦችን ለመቀመር እንደሚያስችል ጠቁመዋል።

ጉባኤው ለተከታታይ ሶስት ቀናት የሚካሔድ ሲሆን የሰው ሰራሽ አስተውሎት ዕድልና ፈተናዎች ላይ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል።

በተጨማሪም ሀገራት የልምድ ልውውጥ እንደሚያደርጉ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.