የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
ህይወት እና ጉዞ

<p>ጃይካ ለኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ እያደረገ ያለውን ድጋፍ እንደሚቀጥል ገለጸ</p>

Mar 4, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ ፤ የካቲት 24/2017 (ኢዜአ)፡- የጃፓን ዓለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) በኢትዮጵያ የግብርና ምርታማነት እና የግብይት ስርዓትን ለማጎልበት እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ።

የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ከጃፓን ዓለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) ምክትል ፕሬዝዳንት ያማጉቺ ሂሮዩኪ ጋር በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።

ውይይቱ ሁለቱ ወገኖች በግብርናው ዘርፍ በጋራ መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው።

ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ጃይካ በኢትዮጵያ በሆርቲካልቸር እና በሌሎች የግብርና መስኮች ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በምግብ ራስን ለመቻል በጀመረችው ጉዞ ሩዝ በስፋት ማምረት መጀመሯንና በዚህም 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን አመልክተዋል።

ለሩዝ ልማት ተስማሚ ስነ-ምህዳር መኖሩን የገለጹት ሚኒስትሩ ጃይካ በሩዝ ልማት ያለውን ልምድ በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግና ቴክኖሎጂን ከማስፋፋት አኳያ የበለጠ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

ሚኒስትሩ 70 በመቶ የሚጠጋው የወጪ ንግድ የግብርና ምርቶች መሆናቸውን ጠቅሰው የግብርና ግብይትን ለማጠናከር ድጋፍ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

የጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) ምክትል ፕሬዝዳንት ያማጉቺ ሂሮዩኪ በበኩላቸው ጃይካ በኢትዮሼፕ በሆርቲካልቸርና በሌሎች ዘርፎች ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

አርሶ አደሮችን ለማበረታታት፣ የሩዝ ልማት ቴክኖሎጂዎችን ለማስፋት እና የባለድርሻ አካላትን አቅም ለማሳደግ እየሰራ ነው ብለዋል።

በቀጣይም የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግና የግብርና ግብይትን ለማጠናከር ድጋፍ እንደሚደረግ አመልክተዋል።

ጃይካ በግብርናው ዘርፍ በተለይም በሆርቲካልቸር እና በሩዝ ልማት፣ በተፈጥሮ ሀብት፣ በአየር ንብረት፣ እንዲሁም በስርዓተ ምግብ እና በግብርና ኢንሹራንስ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር እየሰራ እንደሚገኝ ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.