የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
ህይወት እና ጉዞ

የሃዋሳ ከተማ አምራች ኢንዱስትሪዎች በተኪ ምርቶች አቅርቦት የበኩላቸውን ሚና እየተወጡ ነው

Mar 10, 2025

IDOPRESS

ሀዋሳ፤ የካቲት 30/2017 (ኢዜአ)፦ በሃዋሳ ከተማ የሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎች ከውጭ የሚገቡ ተኪ ምርቶችን በማምረት በውጭ ምንዛሬ ማዳን ረገድ የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን ገለጹ።

"የኢንዱስትሪ ማህበረሰብ እንገነባለን" በሚል መሪ ሃሳብ ከ130 በላይ አምራች ኢንዱስትሪዎች የተሳተፉበት አውደ ርዕይና ባዛር በሃዋሳ ከተማ ተካሂዷል።

ኢዜአ ካነጋገራቸው የዐውደ ርዕይና ባዛር ተሳታፊዎች መካከል የኤልሻሎም ጠቅላላ የኤሌክትሮ መካኒካል ኢንጂነሪንግ ማህበር ሰብሳቢ ጋሻው ኤዶ እንዳሉት ማህበራቸው የእህል መውቂያ፣ የዳቦ መጋገሪያ፣ የስፓርት መስሪያና ሌሎች 15 መሳሪያዎችን ያመርታል።

መሳሪያዎቹ ከውጭ ከሚገቡት ከ50 በመቶ በላይ የዋጋ ቅናሽ ያላቸው በመሆኑ በአነስተኛ ወጪ በሥራ ዕድል ፈጠራ የሚሰማሩ አንቀሳቃሾችን ተጠቃሚ ያደርጋሉ ብለዋል።


የአቤ ሞደፊኬሽን ሥራ ማህበር ሥራ አስኪያጅ ወጣት ገነት አበበ በበኩሏ ማህበሩ ከውጭ የሚገቡ የኮንስትራክሽን፣ የስፖርት መስሪያና የግብርና ማቀነባበሪያ መሳሪያዎችን በአገር ውስጥ በማምረት በዝቅተኛ ዋጋ ለገበያ እያቀረበ መሆኑን ተናግራለች፡፡


"ምርቶቹ በሀገር ውስጥ መመረታቸው ካላቸው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ባሻገር ረዥም ጊዜ የሚያገለግሉ፣ መለዋወጫ እቃ በቀላሉ የሚገኝላቸውና የተጠቃሚውን የመግዛት አቅም ያገናዘቡ ናቸው" ብላለች፡፡

ከኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በኋላ የህብረተሰቡ የሀገር ውስጥ ምርትን የመጠቀም ባህል እየተለወጠ መሆኑን የገለጸችው ወጣቷ፣ በማህበሩ የሚመረቱ ማሽነሪዎች ከውጭ ከሚገቡት ጋር ሲነጻጸሩ የዋጋ ልዩነት እንዳላቸው ተናግራለች።

ለቢሮና ለቤት አገልግሎት የሚውሉ የእንጨት ውጤቶችን በማምረት የውጭ ምንዛሬን ለማስቀረት እየሰሩ መሆኑን የገለጸው ደግሞ የአበራ አብርሃም የፈርኒቸር እቃዎች አምራች ኢንዱስትሪ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ስምኦን ታፈሰ ነው፡፡


ምርቶቻችንን ለመንግስትና ለግል ተቋማት በስፋት በማቅረብ የዘርፉን ኢኮኖሚያዊ አስተዋጾ ከማሳደግ ባለፈ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ጥረት ያለው ምርት እያመረቱ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢንጂነር ስምኦን እንደገለጸው አምራች ኢንዱስትሪዎች በመንግስት የሚደረግላቸው ድጋፍ የማምረት አቅማቸውን እያሳደገው መጥቷል።

አውደ ርዕዩና ባዛሩ መዘጋጀቱ የገበያ ትስስር ለመፍጠርና ቴክኖሎጂን ለማሸጋገር እንደሚያግዝም ተናግሯል፡፡

የሲዳማ ክልል ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ጎሳዬ ጎዳና በበኩላቸው እንዳሉት በክልሉ በተኪ ምርት ማምረት ሥራ ላይ የተሰማሩ ከ75 በላይ ኢንዱስትሪዎች አሉ፡፡

ኢንዱስትሪዎቹ በጨርቃጨርቅ፣ በቆዳና ቆዳ ውጤቶች፣ ኮንስትራክሽን፣ በብረታብረትና በኢንጂነሪንግ ዘርፍ መሰማራታቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

ዘርፉ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት፣ በሥራ ዕድል ፈጠራና በተክኖሎጂ ሽግግር የሚፈለገውን ውጤት እንዲያስገኝ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ለአምስት ቀናት የቆየው የአምራች ኢንዱስትሪዎቹ ባዛርና አውደ ርዕይ ዛሬ ተጠናቋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.