የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
ህይወት እና ጉዞ

በዞኑ በግብርና ኢንሼቲቮች የአርሶ አደሩን ኑሮ ከማሻሻል ባለፈ የሥራ ባህል ለውጥ ማምጣት ተችሏል

Mar 11, 2025

IDOPRESS

አዳማ፤ መጋቢት 1/2017(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን በግብርና ኢንሼቲቮች በዓመት እስከ ሶስት ጊዜ በማምረት የአርሶ አደሩን ኑሮ ከማሻሻል ባለፈ የሥራ ባህል ለውጥ ማምጣት መቻሉን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አባቡ ዋቆ ገለጹ።

በክልል ደረጃ የተቀረፁት የግብርና ኢንሼቲቮች በዞኑ በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሰብል፣ በእንስሳት፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ዘርፎችን በማካተት ተግባራዊ እየተደረጉ መሆናቸውን ዋና አስተዳዳሪው ለኢዜአ ተናግረዋል።

ባለፉት አራት ዓመታት ሲተገበሩ የቆዩት የግብርና ኢንሼቲቮች የአዋሽ ወንዝን ጨምሮ ሌሎች የከርሰ እና የገፀ ምድር ውሃ በመጠቀም መስኖና መደበኛ የእርሻ ስራዎች በስፋት በማከናወን ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።


በተለይ በዞኑ ቆላማ በሆኑት አዳሚ ቱሉ፣ አዳማ፣ ፈንታሌ፣ ቦሰት፣ ቦራ፣ ሉሜ፣ ዱግዳና ሊበን ጨቋላ ወረዳዎች ውሃን ከከርሰ ምድር በማውጣት በበጋ መስኖ ስንዴ፤ አትክትልና ፍራፍሬ እየለማ ነው ብለዋል።

በዚህም ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን ለማሳደግ እንዲሁም ተኪ የግብርና ምርቶችን ለማምረትና ሰፊ የስራ እድል ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑንም አቶ አባቡ ዋቆ ጠቅሰዋል።

ይህም በዓመት ከሁለት እስከ ሶስት ጊዜ በማምረት የአርሶ አደሩን ኑሮ ከማሻሻል ባለፈ የስራ ባህል ለውጥ ማምጣት መቻሉን ገልጸዋል።


በዞኑ እየታረሰ ከሚገኘው መሬት ውስጥ ከ300ሺህ ሄክታር በላይ በበጋ መስኖ ስንዴና በአትክልትና ፍራፍሬ በማልማት 16 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚገኝ ካለፈው ተሞክሮ መረዳት መቻሉንም ጨምረው አመልክተዋል።

ከመስኖ ስንዴ በተጨማሪ በዞኑ የቦሎቄ፣ ሰሊጥ፣ አኩሪ አተርና ማሾ በስፋት በማልማት ባለፉት ስድስት ወራት ከ900ሺህ ኩንታል በላይ ምርት በማዕከላዊ ገበያ በኩል ወደ ውጭ መላኩን ጠቅሰዋል።

ከሁለት ዓመታት በፊት በ29 ሄክታር መሬት ላይ ይለማ የነበረው የሙዝ ልማት በአሁኑ ወቅት ወደ 600 ሄክታር መሬት ማሳደግ መቻሉን ጠቁመዋል።


የአርሶ አደሩ የአኗኗር ዘይቤ በመለወጥ ከባህላዊ አስተራረስ ተላቆ ወደ ሜካናይዜሽን ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑን አመልክተው፤ በዚህም ከሶስት ዓመት በፊት የነበረውን 42 ትራክተሮች ወደ 172 መድረስ መቻሉንም ተናግረዋል።

በምሥራቅ ሸዋ ዞን ከ460 በላይ አርሶ አደሮች በማኑፋካቸሪንግ፣ በአግሮ ኢንዱስትሪና ሰፋፊ እርሻን ጨምሮ ወደ ኢንቨስትመንት መሸጋገራቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.