የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
ህይወት እና ጉዞ

በክልሉ ለትምህርት ተቋማት እየተደረገ ያለው የቴክኖሎጂ ድጋፍ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል - ቢሮው

Mar 15, 2025

IDOPRESS

ባህር ዳር፤ መጋቢት 5/2017(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ተማሪዎችን በእውቀት፣ ክህሎትና አመለካከት እንዲሁም በቴክኖሎጂ የዳበሩ ሆነው እንዲወጡ እየተደረገ ባለው ጥረት የባለ ድርሻ አካላት ድጋፍ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ገለፀ።

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በባህር ዳር ከተማ ለሚገኙ ትምህርት ቤቶች የላፕቶፕ ድጋፍና አነስተኛ ገቢ ላላቸው ወገኖች የጤና መድህን ሽፋን አድርጓል።

የቢሮው የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደግሰው መልሰው በድጋፍ ርክክቡ ወቅት እንዳሉት፤ መጪው ጊዜ የቴክኖሎጂና የዲጂታላይዜሽን ዘመን ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ትውልዱን ማብቃትና ማዘጋጀት ይገባል።

በክልሉ አቅም በፈቀደ መጠን የትምህርት ተቋማትን ከማስፋት ባሻገር በቴክኖሎጂ እንዲደገፉ በማድረግ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የሚያግዙ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ።

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበው ባለድርሻ አካላት ተገቢውን ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባም ተናግረዋል።

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ሙሉዓለም አቤ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ከመጪው ዘመን ጋር ተወዳዳሪ ሆኖ ለመዝለቅ የትምህርት ዘርፉ በላቀ ቴክኖሎጂ የታገዘ ሊሆን ይገባል።

ቴክኖሎጂ የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ፣ በእውቀትና በክህሎት የዳበረ ትውልድን ለመገንባት የጎላ ፋይዳ እንዳለው ጠቅሰው፤ ለዚህም የላቀ ትብብርና መደጋገፍ እንደሚገባ አመልክተዋል።


ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ለትምህርት ቤቶች ያደረገው ድጋፍ ያለባቸውን የቴክኖሎጂ አቅርቦት ከመቅረፍ ባሻገር ተወዳዳሪ ተማሪዎች ለማፍራት ይረዳል ነው ያሉት።

ሳፋሪኮም ኢትዮጰያ የቴክኖሎጂ አቅርቦትን ከማስፋት ባሻገር ለህብረተሰቡ ማህበራዊ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል ያሉት ደግሞ በሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የሰሜን ምስራቅና ምዕራብ የውጭ ግንኙነት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጥላሁን ብርሃኑ ናቸው።

ከዚህ ቀደም በበርካታ አካባቢዎች ድጋፍ መደረጉን አስታውሰው፤ በዛሬው ዕለትም ለሶስት ትምህርት ቤቶች ለእያንዳንዳቸው 10 ላፕቶፕና የዋይ ፋይ አፓራተስ ድጋፍ መደረጉን ገልፀዋል።

እንዲሁም የመክፈል አቅም ለሌላቸው 100 ወገኖች ለአንድ ዓመት የሚቆይ የጤና መድህን ሽፋን መሰጠቱን ጠቅሰው፤ እገዛውና ድጋፉ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.