የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
ህይወት እና ጉዞ

የጤና ጉዳት የሚያስከትል የገበታ ጨው በህገወጥ መንገድ ሲመረት ተያዘ

Mar 17, 2025

IDOPRESS

ሀዋሳ፤ መጋቢት 6/2017 (ኢዜአ)--የጤና ጉዳት የሚያስከትል አዮዲን ያልተቀላቀለበት የገበታ ጨው በህገወጥ መንገድ ሲመረት ተገኝቶ መያዙን የኢትዮጵያ ምግብና መድሀኒት ባለስልጣን ሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

ምርቱ የተያዘው ባለስልጣኑ ከሲዳማ ክልል ጤናና ጤናነክ ግብዓት ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣንና ከተለያዩ የጸጥታ አካላት ጋር ተቀናጅቶ ባደረገው ክትትል መሆኑም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ምግብና መድሀኒት ባለስልጣን ሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ፍቃዱ ንማኔ እንደገለጹት፣ ጽህፈት ቤቱ በሲዳማ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎችና በኦሮሚያ ክልል ስምንት ዞኖችና አምስት የከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም በሶማሌ ክልል ሊበንና ዳዋ ዞኖች የክትትልና ቁጥጥር ስራ ያከናውናል።

በእነዚህ አካባቢዎች ባለፉት ሁለት ወራት በ1ሺህ 800 ተቋማት ላይ የቁጥጥር ሥራዎች ማከናወኑን ጠቅሰው፣ በዚህም ጊዜ ያለፈባቸው፣ መስፈርት የማያሟሉ፣ ያለፈቃድ በመኖሪያ ቤት ጭምር የተመረቱ 42 አይነት የጨውና የተለያዩ ምርቶች ተገኝተው ከገበያ እንዲሰበሰቡ መደረጉን ገልጸዋል።

የጨው ማምረቻ ስፍራና የአመራረት ሂደቱ የንጽህና ችግር ያለበት ከመሆኑ ባለፈ ለቆዳ ፋብሪካ ግብዓትነት የሚውል ጨው በመፍጨት "አይኦዲን አለው" በሚል ታሽጎ ለገበያ ሲቀርብ እንደነበረም ሃላፊው ተናግረዋል።

በቅንጅት በተደረገ ክትትል በለኩና በሃዋሳ ከተሞች ለጤና ጠንቅ የሆነና አዮዲን የሌለው ጨው በግለሰብ ቤት ሲመረት ተገኝቶ መያዙንም ገልጸዋል።

በእዚህም በተለያየ መጠን ታሽጎ የተዘጋጀ ጨው፣ ያልተፈጨ ጥሬ ጨው፣ የማሸጊያ ማሽን፣ የጨው መፍጫ እና የተለያዩ ማሸጊያዎችም አብሮ መያዙን ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ የጤና ጉዳት የሚያስከትሉ ደረጃቸውን ያልጠበቁ ምርቶችን ከመጠቀም እንዲቆጠብ አሳሰብው በማሳያነትም የተወሰኑትን የጨው ምርቶች ገልጸዋል።

የሲዳማ ክልል ጤናና ጤናነክ ግብዓት ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ቡረሶ ቡላሾ በበኩላቸው፣ ደረጃቸውን ያልጠበቁ የጨው ምርቶች ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመሩ መምጣታቸውን በተደረገ ክትትል መረጋገጡን ገልጸዋል።

ለአብነትም ባለፉት ሁለት ወራት በቅንጅት በተከናወኑ ሥራዎች በርካታ የጨው ምርቶችን መያዛቸውን ነው የተናገሩት።

በለኩ ከተማ በመኖሪያ ቤት ውስጥ የተለያዩ ማሸጊያዎችን በመጠቀም በድብቅ የታሸገ ጨው በማዘጋጀት ለገበያ ሲያቀርብ የነበረ ግለሰብም በቁጥጥር ስር ውሏል ብለዋል።

ምንም አዮዲን የሌለውንና ለቆዳ ፋብሪካ የሚውል ጨውን በማስመጣት ፈጭቶ ለገበያ ሲያቀርብ የነበረ ግለሰብ ለህግ በማቅረብ በእስር እንዲቀጣ መደረጉንም ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ አጠራጣሪና የማይታወቁ ምርቶች በገበያ ሲያጋጥመው ለኢትዮጵያ ምግብና መድሀኒት ባለስልጣን ነጻ የስልክ መስመር 8482 ጥቆማ በመስጠት ትብብሩን እንዲያሳይም የሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ፍቃዱ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.