አዲስ አበባ፤ መጋቢት 7/2017(ኢዜአ)፡- በመዲናዋ የአዳዲስና ነባር የቱሪዝም መዳረሻዎች ልማት በከተማዋ አህጉር እና አለም አቀፍ ሁነቶች እንዲካሄዱ ማስቻሉን የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ገለፀ።
በአዲስ አበባ የሚካሄዱ ሁነቶች መበራከት መዲናዋ ለማይስ ቱሪዝም እድገት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ እንደምትገኝ ያሳዩ መሆኑንም ቢሮው ገልጿል።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ ሁንዴ ከበደ ለኢዜአ እንዳሉት ቱሪዝም በሀገሪቱ የረጅም ዘመን ታሪክ ያለው ዘርፍ ቢሆንም ባላት እምቅ ሀብት ልክ ተጠቃሚ ሳትሆን ቆይታለች።
ዘርፉ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የሚጠይቅ መሆኑን ተከትሎ የመሰረተ ልማት ውስንነቶች እንደነበሩም ጠቅሰዋል።
ከለውጡ ወዲህ የቱሪዝም ዘርፍ ትኩረት አግኝቶ ከአምስቱ የኢኮኖሚ ምሰሶዎች አንዱ ተደርጎ እየተሰራበት ያለ መሆኑንም ተናግረዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አነሳሽነት በገበታ ለሸገር፣ ለሀገርና ለትውልድ መርሃ-ግብሮች በርካታ የቱሪዝም መዳረሻዎች ልማት መካሄዱን አንስተዋል።
በአዲስ አበባ ከተማም አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ከማልማት ባለፈ ነባር የቱሪስት መዳረሻዎችን የማደስ ስራ መሰራቱን ጠቅሰዋል።
የወዳጅነት አደባባይ፣ የእንጦጦ እና አንድነት ፓርክን ጨምሮ ሌሎች የቱሪዝም መዳረሻዎች ልማት የቱሪስት ቁጥርን ማሳደግና የቆይታ ጊዜያቸውን ማራዘም የሚያስችሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ይህም የዘርፉን ተዋንያን ተጠቃሚነት የሚያሳድግ መሆኑን ተናግረዋል።
የአድዋ ድል መታሰቢያና የአዲስ አለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ግንባታ ለማይስ ቱሪዝም አስተዋፅኦ የሚያበረክቱ መሆናቸውንም ገልፀዋል።
አዲስ አበባ የበርካታ አህጉር እና አለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ መሆኗን ተከትሎ የተለያዩ ጉባኤዎች እንደሚከናወኑባት አውስተው አሁን ላይ የተሰሩት የቱሪዝም መዳረሻ ልማት ስራዎች የማይስ ቱሪዝምን ማስፋት የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ከ50 በላይ አህጉር እና አለም አቀፍ ሁነቶች በከተማዋ መካሄዳቸውን ጠቁመው ይህም ለማይስ ቱሪዝም እድገት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ እንደምትገኝ ማሳያ ነው ብለዋል።
ቢሮው ከተማዋ ያላትን የማይስ ቱሪዝም እምቅ ሀብት ለማውጣት ክፍል አደራጅቶና የዘርፉ ተዋንያን ስለማይስ ቱሪዝም ያላቸውን ግንዛቤ ለማሳደግ እየሰራ መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል።
ቱሪዝም ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ባሻገር ለገፅታ ግንባታ አስተዋፅኦ የሚያበረክት ዘርፍ በመሆኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ማይስ የጉባኤ፣ የኮንፍረንስ፣ የማበረታቻ ጉዞና የዓውደ ርዕይ ሁነቶችን ያጠቃለለ የቱሪዝም ዘርፍ ነው።
አዲስ አበባ ፤የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት ተገልጋዮች ፋይዳ መታወቂያን ተጠቅመው በዲጂታል አማራጭ ትኬት የሚቆርጡበት አሰራር ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ ጥር 03/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን የለማ የትራንስፖርት ኦፕሬተሮችንና የጭነት ባለቤቶችን የሚገናኝ መተግበሪያ አስጀምሯል። ...
Feb 12, 2025