የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
ህይወት እና ጉዞ

ወሎ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የምርምር ሥራዎች የህብረተሰቡን ችግር የሚያቃልሉ ተግባራት እያከናወነ ነው

Mar 19, 2025

IDOPRESS

ደሴ ፤ መጋቢት 9/2017(ኢዜአ) ፡- ወሎ ዩኒቨርሲቲ በተግባር ተኮር ትምህርት ብቁና ተወዳዳሪ ትውልድ ከማፍራት ባለፈ በተለያዩ የምርምር ሥራዎች የህብረተሰቡን ችግር የሚያቃልሉ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ፡፡

የዩኒቨርሲቲ - ኢንዱስትሪ ትስስር መድረክ ዛሬ በደሴ ከተማ ተካሂዷል፡፡


በመድረኩ ላይ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ሐዋ ወሌ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ተቋሙ ለተግባር ተኮር ትምህርት ትኩረት በመስጠት የትምህርት ጥራቱን ከማረጋገጥ ባለፈ በቴክኖሎጂ የበለጸገ ብቁና ተወዳዳሪ ትውልድ ለማፍራት በቅንጅት እየሰራ ይገኛል፡፡

ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምር በማካሄድም የህብረተሰቡን ችግር በመፍታት ተጠቃሚነቱን ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ ወደ ተግባር የሚቀየሩ በርካታ ምርምሮች እየተሰሩ ነው ብለዋል፡፡

ለዚህም በአካባቢው ከሚገኙ ኢንዱስትሪዎችና ምርምር ተቋማት ጋር ጭምር ትስስር በመፍጠር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችን በማበረታታት ሥራ ፈጣሪ ትውልድ ለማፍራት የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡


በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ የምርምርና የማህበረሰብ ጉድኝነት ጉዳዮች ተጠባባቂ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ሠራዊት ሀንዲሶ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከመማር ማስተማር ሥራቸው በተጓዳኝ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲያደርጉ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም ከኢንዱስትሪዎች እና ከቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት ጋር በማስተሳሰር የማህበረሰቡን ችግር ማቃለል እንዲችሉ፣ ሁለንተናዊ ምርታማነትን እንዲያሳድጉ ሪፎርም ጭምር ተሰርቶ እየተተገበረ ይገኛል ብለዋል፡፡

ተማሪዎች በንድፈ ሀሳብ የሚማሩትን በተግባር በማሳየት በቂ እውቀትና ግንዛቤ እንዲኖራቸው ከዩኒቨርሲቲ ጋር ትስስር መፈጠሩን የተናገሩት ደግሞ በአማራ ክልል መንግስታዊ የልማት ድርጅት የሆነው የብረታብረት ኢንዱስትሪ ማሽን ቴክኖሎጂ ኮምቦልቻ ቅርንጫፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ፋጡማ ይማም ናቸው፡፡


በዚህም የማሽኖችን ተግባርና አሰራር ተረድተው የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲያደርጉ እየተደረገ ነው ፤ ከሥራ ጠባቂነት ሥራ ፈጣሪ መሆን እንዲችሉም ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ ነው ብለዋል፡፡

የኮምቦልቻ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙሉጌታ መኮንን በበኩላቸው፤ ከዩኒቨርሲቲው፣ ከቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ጋር ትስስር በመፍጠር የቴክኖሎጅ እውቀት ሽግግር እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመድረኩ የዩኒቨርሲቲው፣ የዞን፣ የከተማ አስተዳደር፣ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች እንዲሁም በአካባቢው የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች አመራር አባላትና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.