መተማ፤ መጋቢት 9/2017(ኢዜአ)፡- በምዕራብ ጎንደር ዞን በሚገኙ ከተሞች ከ91 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተለያየ የመሰረተ ልማት ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን የዞኑ ከተማና መሰረተ ልማት መምሪያ አስታወቀ።
በዞኑ መተማ ዮሐንስ ከተማ አስተዳደር እየተገነቡ ያሉ የውስጥ ለውስጥ መንገዶችና ሌሎች የመሰረተ ልማት ግንባታዎች በክልሉና በዞኑ ከፍተኛ አመራሮች ተጎብኝተዋል።
የዞኑ ከተማና መሰረተ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ይግለጥ አበባው በጉብኝቱ ወቅት እንዳሉት የመሰረተ ልማት ግንባታው እየተካሄደ የሚገኘው በሶስት ከተማ አስተዳደሮችና አራት መሪ ማዘጋጃ ቤቶች ነው።
በከተሞቹ በህዝብ የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ለመመለስ በተደረገ ጥረት ከክልሉ መንግስት፣ ከህብረተሰቡና ከከተሞቹ በተሰበሰበ 91 ሚሊዮን 75 ሺህ ብር የ24 ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተካሄደ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
እየተገነቡ ከሚገኙት መካከልም የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ፣ የውስጥ ለውስጥ ጠጠር መንገድ፣ አነስተኛ ድልድዮች፣ ዲቾችና የወጣቶች መዝናኛ ማዕከላት ይገኙበታል ብለዋል።
እየተገነቡ ባሉ መሰረተ ልማት ህብረተሰቡ በገንዘብና በጉልበት ከስድስት ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልፀዋል።
በእለቱ ከተጎበኙት ፕሮጀክቶች በመተማ ዮሃንስ ከተማ የተገነባው ከአራት ነጥብ አንድ ኪሎ ሜትር በላይ የውስጥ ለውስጥ የጠጠር መንገድ የህብረተሰቡን ችግር የቀረፈ መሆኑን ማየት ተችሏል ብለዋል።
የአማራ ህዝብ ታሪክ ማዕከል ኃላፊ አቶ አዲሱ በየነ በበኩላቸው ህብረተሰቡን ግንባር ቀደም ተሳታፊ በማድረግ የከተማዋን እድገት ለማፋጠን መትጋት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የህዝቡን የመልማት ጥያቄ ለመመለስ የተጀመረውን ጥረት አጠናክሮ ለማስቀጠል አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግም ተናግረዋል።
የመተማ ዮሃንስ ከተማ ነዋሪ አቶ ግዛቸው አስማማው እንደተናገሩት ከተማዋ የክልሉ ቀደምት ደረቅ ወደብ ብትሆንም የተሟላ ፕላን የሌላት በመሆኑ ማደግ ባለባት ልክ አላደገችም ብለዋል።
አሁን ላይ በከተማዋ የውስጥ ለውስጥ መንገድ እውን ለማድረግ የከተማዋ ህዝብ ያለምንም ካሳ ቤት በማፍረስ ልማቱ እንዲሳለጥ የድርሻቸውን መወጣቱ ይበል የሚያሰኝ ነው ያሉት።
"የሬሳ መውጫ አጥተን የምንቸገርበት ጊዜ ነበር" ያሉት ነዋሪው አሁን ላይ ግን መንገድ መከፈቱ የነዋሪውን ችግር ከማቃለሉም ባሻገር ለከተማዋ ውበት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ተናግረዋል።
በጉብኝቱ ላይም የዞን ከፍተኛ አመራር አባላትና የመተማ ዮሃንስ ከተማ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
አዲስ አበባ ፤የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት ተገልጋዮች ፋይዳ መታወቂያን ተጠቅመው በዲጂታል አማራጭ ትኬት የሚቆርጡበት አሰራር ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ ጥር 03/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን የለማ የትራንስፖርት ኦፕሬተሮችንና የጭነት ባለቤቶችን የሚገናኝ መተግበሪያ አስጀምሯል። ...
Feb 12, 2025