የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
ህይወት እና ጉዞ

በክልሉ ያለውን የመልማት አቅም በመጠቀም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ጥረቶች ውጤት እያመጡ ነው

Mar 19, 2025

IDOPRESS

ቦንጋ፤ መጋቢት 9/2017(ኢዜአ)፡- በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ያሉትን የመልማት አማራጮች ወደ ውጤት በመቀየር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ጥረቶች ስኬታማ መሆናቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) ገለፁ።

ርዕሰ መስተዳድሩ እና ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በካፋ ዞን ጨና ወረዳ የለማ የበጋ መስኖ ስንዴና የአትክልት ልማትን ጎብኝተዋል።


በጉብኝቱ ወቅትም ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት፤ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ክልሉ ያለውን የመልማት አቅም ተጠቅሞ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ጥረቶች አበረታች ውጤት እያመጡ ናቸው።

በተለይም በግብርናው ዘርፍ ሁለንተናዊ ለውጥ በማምጣትና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየተሰራ ያለው ስራ አመርቂ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን ነው ያነሱት።

ለአብነትም በክልሉ የስንዴ ምርት ላይ የተመዘገበውን ውጤት አንስተው የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንደሚሰራ ተናግረዋል።


ለዚህም የመስኖ አማራጮችን ለማስፋት ስራ ትኩረት መሰጠቱን ጠቅሰው ባለፈው ዓመት ተመርቀው ወደ ስራ በገቡ 7 ዘመናዊ አነስተኛ የመስኖ አውታሮች ጥሩ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን መመልከታቸውን ተናግረዋል።

ከእነዚህም ውስጥ በጨና ወረዳ ባለፈው ሐምሌ ወር የተመረቁት የኦፍያና ቄነች የመስኖ አውታሮችን በመጠቀም የአካባቢው አርሶ አደሮችና ወጣቶች የበጋ መስኖ ስንዴና የተለያዩ አትክልቶችን ለማልማት እያደረጉ ያሉት ጥረት የሚበረታታ ነው ብለዋል።


ከዚህ ቀደም በአካባቢው የስንዴ ልማት ተሞክሮ እንደማያውቅ የተናገሩት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፣ አሁን ላይ በክላስተር የለማው 86 ሄክታር የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በጥሩ ቁመና ላይ መሆኑን መመልከታቸውን ጠቁመዋል።

የመስኖ አውታሮችን በተገቢው በመጠቀምና በማስተዳደር የተሻለ ስራ መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል።


የክልሉ መንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ፍቅሬ አማን በበኩላቸው፣ ክልሉ ያለውን እምቅ የመልማት አቅም በመለየት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ ያለው ስራ አበረታች መሆኑን ገልፀዋል።

ከዚህ ቀደም ተሞክሮ በማይታወቅ መልኩ የመስኖ አውታሮችን በመጠቀም የለማው የበጋ መስኖ ስንዴ ውጤታማ መሆኑን አንስተው ወደ ሌሎች አካባቢዎችም የማስፋት ስራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።


በክልሉ በዘንድሮ ዓመት በ2ኛ ዙር በመስኖና በበልግ 103 ሺህ ሄክታር ማሳን በማልማት ወደ 27 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ የተናገሩት ደግሞ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው ናቸው።

በዚህም 5ሺህ 50 ሄክታር ማሳ በበጋ መስኖ ስንዴ መልማቱን ጠቁመው ምርታማነቱንም በሄክታር ከ38 ኩንታል በላይ ለማድረስ መታቀዱንም ጠቁመዋል።

ባለፉት ዓመታት በክልሉ የመስኖ አውታሮችን ለማስፋት በተሰራው ስራ ውጤት መታየቱን ገልፀው፣ ባለፈው ሐምሌ ወር ላይ የተመረቁትን የቄነችና የኦፍያ አውታሮችን በመጠቀም እየለማ ያለው የበጋ መስኖ ስንዴና አትክልት ለሌሎችም አርአያ የሚሆን ነው ብለዋል።

አርሶ አደሮቹ ከዚህ በላይ ጊዜያቸውን በሙሉ ማሳ ውስጥ በማሳለፍ ከሶስት ጊዜ በላይ እንዲያመርቱም አቶ ማስረሻ አሳስበዋል።


በዞኑ የመስኖ አውታሮችን በማስፋት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ ያለው ስራ ውጤት እያመጣ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ፣ ዛሬ የተጎበኙት የአርሶ አደሮቹ ስራም የዚህ ማሳያ ነው ብለዋል።

በጉብኝቱም የክልልና የዞን ከፍተኛ አመራሮች፣ ሞዴል አርሶ አደሮች እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.