አዲስ አበባ፤መጋቢት 30/2017(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ የኢ-ኮሜርስ ግብይት እንዲጎለብት ለዘርፉ ተዋናዮች ምቹ መደላድል መፍጠር የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወነ መሆኑ ተገለጸ።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ የኢ-ኮሜርስ ግብይት ባህል እንዲጎለብት ለማስቻል በተለያየ ዘርፍ ላይ ለሚገኙ የባለድርሻ አካላት ስልጠና ሰጥቷል።
በዚሁ ወቅት የኢ-ኮሜርስ የግብይት እንቅስቃሴ እንዲጎለብት የዘርፉ ተዋናዮች የነቃ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚገባቸውም ተጠቁሟል፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ይሽሩን አለማየሁ (ዶ/ር) ስልጠናውን ባስጀመሩበት ወቅት፤ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ እድገት ያለ ኢ-ኮሜርስ እንቅስቃሴ እውን ማድረግ አዳጋች ነው ብለዋል።
በዘርፉ ያሉ አቅሞችን በማስተባበር ኢትዮጵያ ከኢ-ኮሜርስ ልታገኝ የሚገባትን ጥቅም ለማሳደግ እና ዜጎች ከዘርፉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ምቹ መደላድል የሚፈጥሩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ኢ-ኮሜርስን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚደረገው ጥረት ግብ እንዲመታ የዘርፉን ተዋናዮች ግንዛቤ ማጎልበት አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ያስሚን ወሃብረቢ፥ ኢትዮጵያ ወደ ዲጂታላይዜሽን የምታደርገውን ጉዞ ለማፋጠን ብሄራዊ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ካውንስል ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱን አውስተዋል።
በካውንስሉ ውስጥ የኢ-ኮሜርስ ንዑስ ኮሚቴ መኖሩን ገልጸው፥ ኮሚቴው በኢትዮጵያ ያለውን የኢ-ኮሜርስ እንቅስቃሴ ለማጎልበት የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ኢ-ኮሜርስ ለንግዱ እንቅስቃሴ መሳለጥ የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን በመግለጽ፥ በአምራችና በሸማች መካከል መተማመን ያለው የንግድ ልውውጥ እንዲኖር የሚስችል ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የክፍያ ስርዓት ዳይሬክተር ሰለሞን ዳምጠው፥ በሀገሪቱ የኢ-ኮሜርስ አሰራር እየተለመደ ቢሆንም በማህበረሰቡ ዘንድ ባህል እንዲሆን መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
የአፍሪኮም ቴክኖሎጂ ዋና ስራ አስፈጻሚ ባህሩ ዘይኑ በበኩላቸው፥ ስልጠናው የግሉ ዘርፍ ቀልጣፋ፣ ዘመናዊ እና ጥንቃቄ የተሞላበት የኢ-ኮሜርስ ግብይትን እንዲያሳልጥ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።
አዲስ አበባ ፤የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት ተገልጋዮች ፋይዳ መታወቂያን ተጠቅመው በዲጂታል አማራጭ ትኬት የሚቆርጡበት አሰራር ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ ጥር 03/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን የለማ የትራንስፖርት ኦፕሬተሮችንና የጭነት ባለቤቶችን የሚገናኝ መተግበሪያ አስጀምሯል። ...
Feb 12, 2025